
ባሕር ዳር: ታኅሳስ 3/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በክልሉ ለወራት የዘለቀው ግጭት እንዲቆም እና የሰላም ጥሪ እንዲደረግ የአማራ ክልል ሕዝብ በውይይቶቹ ሁሉ በተደጋጋሚ ሲጠይቅ መቆየቱ ይታወሳል። ከታኅሳስ 02/2016 ዓ.ም ጀምሮ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በግጭቱ ውስጥ የገቡ ሁሉ ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ የሚያስችል የሰላም ጥሪ አድርጓል።
ስለሰላም ጥሪው አተገባበር እና ሕዝቡ እፎይታ ያገኝ ዘንድ የሚኖረውን ፋይዳ በተመለከተ የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ለወራት በዘለቀው ግጭት ሳቢያ በክልሉ ሕዝብ ላይ በርካታ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ደርሷል፤ ይህንን ችግር በአስቸኳይ በመፍታት በአንድነት ለልማት መቆም ያስፈልጋልም ብለዋል።
ቢሮ ኀላፊው “የሰላም ጥሪው የታጠቁ ኃይሎች ለራሳቸው እና ለሕዝብም ሲሉ ሰላምን እንዲመርጡ እና ምህረት እንዲደረግላቸው እድል የሚሰጥ ነው” ብለዋል። አለመግባባቶች በንግግር እንዲፈቱ የሚያስችል ስለመኾኑም አብራርተዋል።
የሰላም ጥሪው ግጭት እና ውድመት እንዲቆም፣ በማኅበረሰቡ መካከል መደማመጥ እንዲሰፍን እንዲሁም መረጋጋት እና ልማት እንዲመጣ የሚያስችል እንደኾነም ተናግረዋል። የክልሉ መንግሥትም ይኽንኑ የተሻለ አማራጭ በመከተል እና የሕዝብን እፎይታ ከልብ በመሻት የሰላም ጥሪውን ስለማድረጉ ገልጸዋል።
አቶ ብርሃኑ ስለሰላም ጥሪው አተገባበርም ማብራሪያ ሰጥተዋል። የሰላም ጥሪው በሰባት ቀናት ውስጥ ተግባራዊ እንዲደረግ ነው ቀን የተቆረጠለት። በዚህ ጊዜ ውስጥ ጥሪውን ተቀብለው ሰላምን የሚመርጡ አካላት በአግባቡ አቀባበል ይደረግላቸዋል ብለዋል ቢሮ ኀላፊው። በቀጣይም ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው ሰላማዊ ሕይዎት እንዲመሩ የሚያስችል ሥልጠና እንደሚሰጣቸው አመላክተዋል።
የሰላም ጥሪውን የተቀበሉ አካላት የፈጸሟቸው ወንጀሎች ሊኖሩ ቢችሉ እንኳን የምሕረት እድል ተጠቃሚ መኾናቸው የተረጋገጠ ስለመኾኑም ኀላፊው ተናግረዋል። ከዚህ በፊት በሕግ ተይዘው የተጀመሩ ምርመራዎች ካሉም በምህረት ማዕቀፉ ተካትተው የሚቀሩ ይኾናል ብለዋል። ይህም የሰላም ጥሪውን የተቀበሉ ወጣቶች ወደ ማኅበረሰቡ ገብተው በሰላም እንዲኖሩ እና የበደሉትን ሕዝብም በልማት እንዲክሱ እድል የሚሰጥ ስለመኾኑ አብራርተዋል።
“መሣሪያን አማራጭ አድርገው የወጡ አካላት የተለያዩ ወንጀሎችን ፈጽመዋል፤ አሁንም እየፈጸሙ እንደኾነ ይታወቃል፤ እነዚህ አካላት ለሕዝብ ሰላም ሲልባል በምህረት የሚጠቀሙበት እድል መመቻቸቱ መንግሥት ለሰላም ያለውን ቁርጠኛ አቋም የሚያሳይ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
የሰላም ጥሪው ተሳክቶ ክልሉ ሰላም እንዲኾን እና ሕዝቡም እፎይታ እንዲያገኝ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም ኀላፊው ጠይቀዋል። የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ እናቶች፣ ተሰሚነት ያላቸው እና ሰላም ወዳድ የኾኑ ዜጎች በሙሉ የተሳሳቱ ወጣቶችን በመምከር ወደ ሰላም ማምጣት እና የሚጠፋውን ሕይወት እና ንብረት መታደግ አለባቸው ብለዋል።
ጥሪውን ተቀብለው ወደ ማኅበረሰቡ የተቀላቀሉ ወጣቶችን ወንጀል ከፈጸሙበት ግለሰብ፣ ቡድን ወይም ማሕበረሰብ ጋር የማሸማገል እና ሰላም የማውረድ ሥራም በትኩረት መከናወን እንዳለበትም ገልጸዋል። ይህ ሲኾን በሰላም እንዲኖሩ እና ሠርተው እንዲቀየሩ ያደርጋል፤ የክልሉ ሕዝብም እፎይታን አግኝቶ ወደ ልማቱ እንዲገባ ያስችላል ነው ያሉት የፍትሕ ቢሮ ኀላፊው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!