”የታወጀውን የሰላም ጥሪ ተግብረን ወደ ከተማችን ልማት እንመለስ”

40

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 3/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በአማራ ክልል የተከሰተውን የሰላም መደፍረስ ለመፍታት የክልሉ መንግሥት ያደረገውን የሰላም ጥሪ ለማስተግበር የከተማ መዋቅሩን አወያይቷል።
የውይይቱ ዓላማ ከተማ አሥተዳደሩ የሰላም ጥሪውን ለመተግበር ፈጥኖ ወደ ሥራ እንዲገባ ግልጸኝነት መፍጠር መኾኑ ተጠቅሷል።

በውይይቱ የአማራ ክልል መንግሥት ግጭት ውስጥ ለገቡ ኃይሎች የሰላም ጥሪ ማድረጉ ሕዝቡ ሲጠይቀው የነበረ በመኾኑ እፎይታ የሚሰጥ እንደኾነ ተነስቷል። የሰላም ጥሪው ሲተገበርም በውጤታማነት እንዲዘልቅ መደረግ ያለባቸው ቅድመ ዝግጅቶች ተጠቁመዋል።

የሰላም ጥሪው መንግሥት ለሕዝቡ ጥያቄ ጆሮ ሰጥቶ የሰጠው ምላሽ በመኾኑ ሕዝቡ ሰላሙን እንዲያገኝ ያስችለዋል በተባለበት ውይይት የከተማ አመራሩም ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ ተገልጿል።

የእርስ በርስ ግጭቱ ከማንም በላይ እየጎዳ ያለው ሕዝቡን ሰለኾነ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በሰላም ጥሪው ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲኾኑም ተጠይቋል።

የባሕር ዳር ከተማ ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ የሰላም ጥሪው ለሰላም ሲባል ጥፋቶች ይቅር ተብለው የተደረገ ጥሪ መኾኑን ጠቅሰው በፍጥነት መተግበር አለበት ብለዋል። ወደ ሰላሙ ለሚመለሱ ኃይሎች የሥራ ዕድል ፈጠራውንም ኾነ የማቋቋሙን ሥራ ለመሥራት ባሕር ዳር ከተማ ብዙ አማራጮች እንዳሉት ተናግረዋል።

የባሕር ዳር ከተማ ብልጽግና ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞላ ሁሴን የክልሉ መንግሥት የሕዝቡን የሰላም ፍላጎት መሠረት አድርጎ ለታጣቂ ኃይሎች የሰላም ጥሪ ማድረጉን ገልጸዋል። ”የሰላም ጥሪው የፖለቲካ ዓላማ እና ግብን በሰላማዊ መንገድ መፈጸም እንደሚቻል ስለሚጠቅስ ለሕዝቡም ይህንን ማሳወቅ ይገባል” ብለዋል።

ባሕር ዳር ከተማ በዚህ ወቅት የነበራት ልማት ከፍተኛ ነበር ያሉት አቶ ሞላ ”የታወጀውን የሰላም ጥሪ ተግብረን ወደ ከተማችን ልማት እንመለስ” ብለዋል። የሰላም ጥያቄውን መንግሥት እየመለሰ ስለኾነ ሕዝቡም ይህንን ተገንዝቦ ለሰላሙ መስፈን እንዲረባረብ አሳስበዋል።

በከተማዋ የሰላም ጥሪውን ለመተግበር የሎጀስቲክስ፣ የሕዝብ ግንኙነት እና የሰላም ጥሪ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጥሪውን በፍጥነት ለማስፈጸም ዝግጅት መደረጉም በውይይቱ ተገልጿል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደቡብ ጎንደር ዞን በሊቦ ከምከም ወረዳ እና በአዲስ ዘመን ከተማ ከ300 በላይ የቀድሞ ልዩ ኀይል አባላት መንግሥት ያቀረበላቸውን ጥሪ መቀበላቸውን ገለጹ።
Next articleኢትዮጵያ ታምርት፣ እኛም እንሸምት” የተሰኘ የአምራች ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽንና ባዛር በአዲስ አበባ ተከፈተ።