
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን በየወረዳው እና በየደረጃው የሚደረጉ የሕዝብ ውይይቶች ለውጥ ማምጣት ጀምረዋል።
በተከታታይ በተደረጉ ውይይቶች እና መንግሥት ባደረገው የሰላም ጥሪ በየአካባቢው ባልተገባ መንገድ ተበትነው የነበሩ የቀድሞ የአማራ ልዩ ኀይል አባላት የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው መንግሥት በሚያመቻችላቸው ሁሉ ተሰልፈው ክልሉን ከገጠመው የጸጥታ ችግር ለማውጣት እንደሚሠሩ ነው የተናገሩት።
የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ እና የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች የቀድሞ ልዩ ኀይል አባላቱን በአዲስ ዘመን ከተማ ተቀብለው አወያይተዋል።
የቀድሞ ልዩ ኀይል አባላቱም “በተሳሳተ መረጃ ባልተገባ መንገድ ብንበተንም አሁን መንግሥት ያቀረበልንን ጥሪ ተቀብለን የሚሰጠንን ግዳጅ በብቃት ለመፈጸም ዝግጁ ነን” ብለዋል።
“በሠለጠንበት ሙያ ለጸጥታ ኀይሉ ተጨማሪ አቅም በመኾን አሁን ላይ የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ለማስተካከል በቁርጠኝነት እንሠራለን” ነው ያሉት።
ትናንት የሞቱለት ሕዝብ ዛሬም ከገጠመው ችግር ለማሻገር አቅምም ኾነ ቁርጠኝነቱ ዛሬም እንዳላቸው አስረድተዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ “ዛሬ ነገ ሳንል የቀድሞ ልዩ ኀይል አባላቱን በሥልጠና እና በትጥቅ በመደገፍ ሕግ የማስከበር ሥራውን በጋራ እንሠራለን” ብለዋል።
በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በተሳሳተ መንገድ ስትጓዙ ለነበራችሁ ሁሉ የዞኑም ይሁን የክልሉ መንግሥት ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት በደስታ ተቀብሎ በምትፈልጉት መንገድ ያደራጃችኋል ሲሉም ተናግረዋል።
የቀድሞ ልዩ ኀይል አባላቱ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎችም የክልሉ መንግሥት መልስ ለመስጠት ይሠራል ብለዋል።
አሁንም ቢኾን በተለያየ ሁኔታ ላይ ያሉ የቀድሞ ልዩ ኀይል አባላት መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው የሕዝባቸውን እና የክልላቸውን ሰላም እንዲያረጋግጡም ጥሪ አቅርበዋል።
ዋና አሥተዳዳሪው ለቀድሞ ልዩ ኀይል አባላቱ ከዛሬ ጀምሮ የሰላም አምባሳደር ኾናችኋልም ብለዋቸዋል።
በአጭር ጊዜ ውስጥ የፖለቲካ እና ወታደራዊ የተሀድሶ ሥልጠና በመስጠት ለተልእኮ ዝግጁ እንደሚያደርጓቸውም አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፡-ጌታቸው ገደፋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!