የክልሉ መንግሥት ለሰባት ቀናት የሚቆይ የሰላም ጥሪ አስተላለፈ፡፡

434

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ለወራት የዘለቀው ግጭት በርካታ ሰብዓዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ቀውሶችን አስከትሏል፡፡ የተፈጠረውን የሰላም መደፍረስ ተከትሎ በክልሉ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ የህልውና ስጋቱን ቀንሷል ቢባልም በክልሉ የደረሰው እና እየደረሰ ያለው ችግር ዘርፈ ብዙ የሚባል ነው፡፡

የክልሉ ሕዝብ በግጭት ውስጥም ኾኖ በተደጋጋሚ ከክልሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ጋር ባደረጋቸው ውይይቶች ችግሩን በዘላቂነት ለመቋጨት የሚያስችል ሰላማዊ አማራጮች እንዲታዩ ጠይቋል፡፡ የክልሉ መንግሥት ዛሬ ባወጣው መግለጫም ለወራት የዘለቀው የሰላም እና የፀጥታ ችግር ለመጨረሻ ጊዜ እንዲቋጭ የሚያስችል እና ለሰባት ቀናት የሚቆይ የሰላም ጥሪ ማስተላለፉን አስታውቋል፡፡

የክልሉን መንግሥት የሰላም ጥሪ አስመልክቶ በጽሕፈት ቤታቸው መግለጫ የሰጡት የአማራ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) በክልሉ ያለው የጸጥታ ኹኔታ በእጅጉ እየተሻሻለ መጥቷል ብለዋል፡፡ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ይበልጥ ለማጽናት የሰላም ጥሪ ማድረግ አስፈልጓል ያሉት ቢሮ ኀላፊው በተሳሳተ መልኩ የጥፋት መንገድን የመረጡ አካላት ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ ያግዛል ብለዋል፡፡

በክልሉ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በርካታ ጉዳቶች ደርሰዋል ያሉት ዶክተር መንገሻ የክልሉ መንግሥት በቀውስ ውስጥም ኾኖ ከሕዝብ ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን እንዳደረገ አንስተዋል፡፡ በተደረጉ ሕዝባዊ ውይይቶች ሕዝቡ የሰላም አማራጮች ቅድሚያ እንዲታዩ ጠይቋል ነው ያሉት፡፡ ተጨማሪ ጥፋት፣ ደም መፋሰስ እና ውድመትን ለማስቀረት መንግሥት በሆደ ሰፊነት የሰላም አማራጮችን ተመልክቶ ጥሪ አድርጓል ብለዋል፡፡

የፖለቲካ አጀንዳ እና ጥያቄዎች መልስ የሚያገኙት በኃይል አማራጭ ሳይኾን በሰላማዊ ውይይት እና ምክክር ነው ያሉት ቢሮ ኀላፊው መንግሥት የሰላም ጥሪውን ተቀብለው የሚገቡ ኃይሎች ከተሃድሶ ማግስት ለክልሉ ሰላም እና መረጋጋት ጉልበት ይኾናሉ ብሎ ያምናል ብለዋል፡፡ የሰላም ጥሪውን የሚቀበሉ ታጣቂዎች በተከታታይ ሰባት ቀናት ውስጥ በየአሉባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ የኮማንድ ፖስት ዕዞች እንዲያሳውቁ ጥሪ ተላልፏል፡፡

የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ለሚመጡ ታጣቂዎች የኮማንድ ፖስቱ አመራሮች፣ ከክልል እስከ ቀበሌ የሚገኙ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት እና ሕዝቡ ድጋፍ እና ትብብር እንዲያደርግ ትዕዛዝ ተላልፏልም ተብሏል፡፡ ነገር ግን የተላለፈውን የሰላም ጥሪ ቸል በማለት በአመጽ እና የሽብር ተግባር ውስጥ በሚገቡ ግለሰቦች እና ታጣቂዎች ላይ ሕግ የማስከበር እርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዳር 30/2016 ም.አ ቺርቤዋ ጋዚቲ
Next articleበደቡብ ጎንደር ዞን በሊቦ ከምከም ወረዳ እና በአዲስ ዘመን ከተማ ከ300 በላይ የቀድሞ ልዩ ኀይል አባላት መንግሥት ያቀረበላቸውን ጥሪ መቀበላቸውን ገለጹ።