
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በክልሉ ግጭት እንዲያበቃ እና አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የሰላም ጥሪ አቅርቧል።
የሰላም ጥሪዉ ሙሉ መልእክት ቀጥሎ ቀርቧል።
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሕዝብን ፀጥታ እና ደኅንነት አደጋ ላይ የጣለውን ሕገ-ወጥ የኅይል እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር እና ለመቀልበስ በጀግናው የመከላከያ ሠራዊት፣ በክልሉ የፀጥታ ኀይሎች እና በክልሉ ሕዝብ በተከፈለው ክቡር መስዋዕትነት በክልሉ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓትን መታደግ በመቻሉ እና በክልሉ ያለው የፀጥታ ኹኔታ በእጅጉ እየተሻሻለ በመምጣቱ፤ የክልሉን ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት በማፍረስ ክልሉን ከፌደራል መንግሥት በመነጠል የትርምስ ቀጣና ማድረግ ግቡ የነበረውን እንቅስቃሴ ለማክሸፍ እና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በክልሉ የፀጥታ ኃይሎች እና በሕዝብ ርብርብ በተወሰዱ እርምጃዎች በክልሉ የሚታየው የሠላም ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ በእጅጉ እየተሻሻለ የመጣ በመኾኑ እና ይህንን አንፃራዊ ሰላም ይበልጥ ለማጽናት የሰላም ጥሪ ማድረግ በማስፈለጉ፤
በጽንፈኝነት የተቃኘ እና የግል ፍላጎትን ማዕከል ያደረገ አላማ ባነገቡ ጥቂት ግለሰቦች እና ቡድኖች ቅስቀሳ የተሳሳቱ ወጣቶች እና የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከስህተት መንገድ የሚመለሱበትን ሰላማዊ መንገድ ማመቻችት ስለሚገባ፤
በክልሉ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ከሕዝብ ጋር በተደረጉ ተከታታይ ውይይቶች የሕግ የበላይነትን ባረጋገጠ አግባብ ለታጣቁ አካላት የሰላም ጥሪ ቀርቦ ግጭቱ እንዲያበቃ እና አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ከሕዝብ የተነሳውን ጥያቄ በመቀበል፤
ተጨማሪ ደም መፋሰስን፣ጥፋትን እና ውድመትን ለማስቀረት መንግሥት በሆደ-ሰፊነት የሰላም አማራጮችን አሟጦ የመጠቀም ጥረቱን ማስቀጠል ለሃገር እና ለሕዝብ ያለውን ጠቀሜታ ከግምት በማስገባት፤
የፖለቲካ አጀንዳ እና ጥያቄዎች በሰላማዊ እና ሕጋዊ መንገድ ብቻ ዘላቂ መፍትሔ እንደሚያገኙ በፅኑ በማመን እና ለሰላማዊ የፖለቲካ ውይይት እና ምክክር መንገድ የሚጠርግ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን በማመን፤
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መመርያ ዕዝ ጋር በመመካከር ስምምነት በተደረሰበት አቅጣጫ እና የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ የወጣውን የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6 /2015 አንቀጽ 5(4) (ሠ) እና 6(12) መሰረት በማድረግ ይህ የሰላም ጥሪ የውሳኔ ሃሳብ ተላልፏል።
የውሳኔ ነጥቦች፣
1) ይህ ጥሪ ለሕዝብ ይፋ ከተደረገ ጀመሮ በሚቆጠር ሰባት ቀናት ውስጥ በየትኛውም ኢመደበኛ አደረጃጀት እና ትጥቅ ትግል ውስጥ በመንቀሳቀስ ላይ ያሉ ታጣቂዎች ባሉበት አካባቢ በሚገኙ የኮማንድ ፖስት አዛዦች ለዚሁ አላማ ለይተው ለሕዝብ ወደሚያሳውቋቸው የመሰብሰቢያ ስፍራዎች በመሄድ ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ ያላቸውን ፍላጎት እንዲያሳውቁ ጥሪ ቀርቧል።
2) በየአካባቢው ያሉ የቀጣና ኮማንድ ፖስት አመራሮች፣ የአካባቢው አሥተዳደር እና የፖለቲካ አመራሮች እንዲሁም የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍል ተወካዮች እና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመተባበር ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ ፍላጎት ኖሮዋቸው ወደ መሰብሰብያ ስፍራዎች ከላይ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ የሚመጡትን ሁሉ በአግባቡ በመቀበል፣ የህክምና አገልግሎት እና መሰል አጣዳፊ አገልግሎት ለሚያስፈልጋቸውም አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ እንዲያስተናግዱ እና ወደተሃድሶ ማዕከላት እንዲወሰዱ መመሪያ ተሰጥቷል።
3) የቀጣና ኮማንድ ፖስት አመራሮች እና ተሃድሶ ማዕከላት አስተባሪዎች ወደ ሰላማዊ ኑሮ የሚመለሱ የቀድሞ ታጣቂዎች በተሃድሶ ማዕከላት ውስጥ አስፈላጊውን የተሃድሶ ሥልጠና እንዲያገኙ፣ ወደ ማኅበረሰቡ ተቀላቅለው በሰላም ለመኖር የሚያስችላቸውን የአዕምሮ ዝግጅት ለማድረግ አስፈላጊው የሥነ-ልቦና፣ ምክር እና ሌሎች አስፈላጊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ በማድረግ የተሃድሶ መርሐ ግብር መጨረሳቸውን እያረጋገጡ የምስክር ወረቀት እንዲሰጡ መመሪያ ወርዷል።
4) ለሕግ እና ፍትሕ አካላት የተሃድሶ መርሐ ግብር ማጠናቀቂያ የምስክር ወረቀት ያገኙ የቀድሞ ታጣቂዎች በግጭቱ አውድ ውስጥ የተፈጸሙ በምሕረት ሊሸፈኑ የሚችሉ ወንጀሎችን በተመለከተ የምሕረት ተጠቃሚ እንደኾኑ በመገንዘብ እነዚህ ግለሰቦች ላይ ከነዚህ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ የተጀመሩ የምርመራ፣ የክስም ሆነ የፍርድ ማስፈጸም ሂደቶችን በማቋረጥ ተገቢውን ትብብር እንዲያደርጉ መመሪያ ተላልፏል።
5) የክልል፣ ዞን፣ ወረዳ እና ቀበሌ የፖለቲካ፣ የአሥተዳደር አካላት እና አመራሮች ይህን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ለሚመለሱ የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ኑሮ መመለስ እንዲችሉ ተገቢውን ትብብር እንዲያደርጉ፣ በተለይም እነዚህ ዜጎች በሰላማዊ እና ሕጋዊ አግባብ የፖለቲካ ግብ እና አጀንዳቸውን ማራመድ ይችሉ ዘንድ ምቹ አውድ እና የውይይት መደረኮችን እንዲያመቻቹ መመሪያ ተሰጥቷል።
6) ይህንን የሰላም ጥሪ በየደረጃው ካሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እዞች ወይም ኮማንድ ፖስቶች ጋር በመቀናጀት እንዲያስፈጽም እና ለአፈጻጸሙ አስፈላጊ የኾኑ ዝርዝር መመሪያዎችን እንዲያወጣ ለክልልሉ የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊነት እና ሥልጣን ተሰጥቷል።
7) የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መመሪያ እዙ ጋር በመተባበር ይህ የሰላም ጥሪ ተግባራዊ ኾኖ በክልሉ ግጭት እና ሁከት እንዲቀር፣ ሕዝብም እፎይታ እንዲያገኝ ያለውን ቁርጠኝነት እየገለፀ ለዚህ ጥሪ ውጤታማነት አስተዋፅዖ ሊያበረክቱ የሚችሉ ባለድርሻ አካላት ሁሉ፣ በተለይም የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ለሰላም አጀንዳው መሳካት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪውን ያቀርባል።
በዚሁ አጋጣሚ ይህን ጥሪ ቸል በማለት የአመፅ እና የጉልበት መንገድ በሚመርጡ ግለሰቦች እና ታጣቂዎች ላይ የተጀመረው የሕግ ማስክበር እርምጃ ተጥናክሮ እንደሚቀጥል ለማሳወቅ እንወዳለን።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
ታህሳስ 02/2016 ዓ. ም
ባሕርዳር፣ ኢትዮጵያ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!