የእቴጌ ጣይቱ ብጡል መታሰቢያ ሃውልት በደብረ ታቦር ከተማ ሊገነባ ነው፡፡

641

የንጉሠ ነገሥት ሚስት እና የንጉሥ ባለሟል፤ የሴት ባለመላ እና ባለሙያ፤ የጦር ሜዳ ፈርጥ እና ሕግ አዋቂ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ቆርቋሪና መሥራች ናቸው፡፡ በቅፅል ስማቸው ‹‹ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ›› እቴጌ ጣይቱ ብጡል፤ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ የጎላ ስም ካላቸው ሴቶች ግንባር ቀደምቷ ናቸው፡፡
የዘር ሐረጋቸው ማሩ ቀመስ ደንቢያን በደጃች ማሩ፣ በስሜን ከደጃዝማች ኃይለማሪያም፣ ከላስታና ዋግ በዋግ ሹም ክንፉ፣ ከትግራይ በደጃዝማች ገብረሚካኤል፣ በጎጃም ከደጃዝማች ዮሴዴቅ ይመዘዛል፡፡ በወሎ ደግሞ ቅድመ አያታቸው የዘመነ መሳፍንቱ እውቅ የወረሴህ መስፍን ራስ ጉግሳ ሙርሳ የተንሰላሰለ ነው፤ ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ ብጡል፡፡

የትውልድ ቦታቸው እና ጊዜው ደግሞ ከአጅባር ሜዳ ራስጌ፣ ከደብረ ታቦር ኢየሱስ ግርጌ፣ ከዘመናዊቷ የኢትዮጵያ ማኅፀን አሻጋሪ፣ ከጉና ተራራ ወዲህ ማዶ ሰመርንሃ ጥግ ስር በደብረ ታቦር ነሐሴ 12 ቀን 1832 ዓ.ም እንደነበር ይነገራል፡፡
እቴጌ ጣይቱ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ምሥረታ ጉልህ ሚናና ድርሻ ቢኖራቸውም የዚህ ትውልድ አበርክቷቸውን በመዘከር ግን ውስንነቶች እንደነበሩ ይነገራል፡፡ ይህ አለመታወስ የሚሰማቸው አንድ ኢትዮጵያዊ የእቴጌይቱን ማስታወሻ ሃውልት በትውልድ ቦታቸው ለማቆም ቦታ ተረክበው የመሠረተ ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡ ‹‹ትውልዱ ካለፉት ቅድመ አያቶቹ ታሪክ ይማር ዘንድ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ ጥያቄውን በአንድ ቀን ተቀብለን አስተናግደናል›› ያሉት የደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አበበ እምቢአለ ናቸው፡፡ ለግንባታው መሳካትም የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል፡፡
ከ38 ዓመታት በላይ ኑሯቸውን በውጪ ያደረጉት አቶ ደህናሁን እምሩ ደስታ ‹‹እቴጌይቷ በመሠረቷት ከተማ አዲስ አበባ ሃውልቱን ለማቆም ቀድሞ እንደታሰበ እና እንቅስቃሴ ቢጀምርም በተለያየ ምክንያት ባለመሳካቱ የሃውልቱን ግንባታ በትውልድ አካባቢያቸው ለማድረግ አስቤያለሁ›› ብለዋል፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ለሚከበረው 125ኛ ዓመት የዓድዋ ድል በዓል ሃውልቱ ተጠናቅቆ ይመረቃል፡፡ ግንባታውን የሚከታተል ኮሚቴ እና ለሥራው ማስጀመሪያ የሚሆን ገንዘብ በባንክ ገቢ መደረጉም ታውቋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

Previous articleበኩር የካቲት 09/2012 ዓ/ም
Next articleባለስልጣኑ የጎንጂ-ቆለላን ጨምሮ አራት የመንገድ ፕሮጀክቶችን ውል ተፈራረመ፡፡