
ደሴ: ታኅሳሥ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ አዘጋጅነት ከምሥራቅ አማራ የሃይማኖት አባቶች፤ የሀገር ሽማግሌዎች እና መሪዎች ጋር የሰላም የምክክር መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ እያተካሄደ ነው።
የምክክር መድረኩ በተለያዩ የሃይማኖት አባቶች አማካኝነት ለሀገር ሰላም ፀሎት በማድረስ ነው የተጀመረው፡፡
በመድረኩ የተገኙት የኮምቦልቻ ከተማ ከንቲባ ሙሐመድአሚን የሱፍ ለሃይማኖት አባቶች እና ለሀገር ሽማግሌዎች “ሕዝባችን ያደምጣችኋል፤ እናንተ የሀገር ምልክቶች ናችሁና ያጋጠመንን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሚናችሁ ከፍተኛ ነው” ብለዋል።
የምክክር መድረኩ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እየተስተዋለ ያለውን የፀጥታ መደፍረስ እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመጣውን አንፃራዊ ሰላም ለማጽናትና ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ዓላማ ያደረገ መኾኑም ተገልጿል።
በመድረኩ የሰላምን አስፈላጊነት፣ የአማራ ክልልን አሁናዊ የፀጥታ ሁኔታ እና እየደረሱ ያሉ ጉዳቶችን በተመለከተ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በእሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) የመነሻ ጽሑፍ ቀርቧል።
በምክክሩ ማብቂያ ላይ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ በንግግር ይፈቱ ዘንድ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ዘጋቢ፡- ጀማል ይማም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!