
ከእነ ብዙ ሕልሞቹ፣ ከእነ ብዙ ዕቅዶቹ ሳያስበው ይህችን ዓለም ተሰናበታት ይሉታል ጎደኞቹ። የሚሳሳላቸው ልጆቹን፣ ነገ አደርጋቸዋለሁ ያላቸውን እቅዶቹን ድንገት ተሰናብቷቸው ሄደ። ኖሮ መሥራትን፣ ኖሮ ማገልገልን ነበር የእሱ ህልም።
ወዳጅ ዘመዶቹ፣ ጓደኞቹ እና የሥራ ባልደረቦቹ ቶሎ ተሽሎት ወደ ሥራ መመለስን፣ እቅዶችን መከወነን፣ ራዕዮቹን መኖሩን ይመኝ ነበር እንጂ እሞታለሁ ብሎስ አላሰበው ነበር ይሉታል።
ብዙዎች የሚወዱት፣ በሰላምታው፣ በተግባቦቱ የሚማረኩለት ይርጋዓለም አስማማው የትውልድ ዘመኑ ኅዳር 16 1978 ዓ.ም ነበር። አባቱ አስማማው ጀምብሬ፣ እናቱ ንፁሕ አረጋ ይሰኛሉ። ሰው አክባሪዎች፣ ቅንና ደጋጎች ነበሩ። እነኚህ ደጋጎች በወረኃ ሕዳር በ16ኛው ቀን መልከ መልካም ልጅ ተሰጣቸው።
ይርጋለም ለዓመታት በእናት እቅፍ ማደግን፣ ከእናት ጋር ደስ እየተሰኙ መኖርን አልታደለም። እናቱ በለጋ እደሜው በሞት ተነጠቁበት። ላይሰጥ አይነሳም እንደተባለ እናቱን በሞት ባጣ ዘመን ቀሪ ቤተሰቦቹ እና ጎረቤቶቹ በእንክብካቤ አሳደጉት ይላሉ ዘመዶቹ።
በቤተሰቦቹ እና በጎረቤቶች ሲያሳድጉት መልካምነትን፣ ቅንነትን እና ሰው ወዳድነትን እያስተማሩት፣ ከራስ በላይ ለሌሎች ማሰብን እያሳዩት ነበር። እርሱም አተዳደጉን በተግባር የኖረ፣ በልጅነቱ ለቤተሰቦቹ፣ ለጎረቤቶቹ፣ በታዛዥነቱ፣ በቅንነት ያደገ መልካም ልጅ እንደነበር ታሪኩ ያስረዳል። በመልካም ሥነ ምግባር የታነፀ እንደነበርም ይነገርለታል።
ሩቅ አላሚው ቅርብ አዳሪው ጋዜጠኛ ዕድሜው ለትምህርት በደረሰ ዘመን ወደ አፄ ሠርፀ ድንግል አንደኛ እና መለሰተኛ ትምህርት ቤት በማቅናት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ተከታትሏል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ ወደ ጣና ሐይቅ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታተለ። በዚህም ትምህርት ቤት ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት በማስመዘገብ የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀለ።
ይርጋዓለም አስማማው በ1997 ወደ ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ በመግባት በጋዜጠኝነት ኮምዩንኬሽን የመጀመሪያ ድግሪውን ተቀብሏል። ለትምህርት ታላቅ ጉጉት የነበረው ይርጋዓለም የሁለተኛ ድግሪውንም በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ በባሕል ጥናት በ2015 ዓ.ም በከፍተኛ ውጤት ተመርቋል።
ታታሪው ጋዜጠኛ በትምህርት ያገኘውን እውቀት በመጠቀም ሕዝቡን እና ሀገሩን የተለያዩ የሙያ ዘርፎች እና የሥራ ኃላፊነት አገልግሏል። ለአብነትም ከመጋቢት 22/2001 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 30 2003 ዓ.ም ድረስ በሰሜን ሸዋ ዞን መንዝ ላሎ ወረዳ በኮምዩንኬሽን ፅሕፈት ቤት የፕረስ ሥራዎች ዜና እና ፕሮግራም የሥራ ሂደት አስተባባሪ፣ ከሕዳር 01/2003 እስከ መጋቢት 30 /2003 ዓ.ም በባለሙያነት ሕዝብን አገልግሏል።
ምንጊዜም ራሱን ለተሻለ ነገር የሚያዘጋጀው ትጉህ ጋዜጠኛ ይርጋዓለም ከሚያዚያ 5 /2003 ዓ.ም ጀምሮ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽንን በመላቀቀል ሕይወቱ እስካለፈችበት ጊዜ ድረስ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች አገልግሏል።
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የቴሌቪዥን እና የሬድዮ ዜና አንባቢነት፣ በዜና እና ፕሮግራም ዘጋቢነት ሠርቷል። በሥራ ውጤታማነቱ ከአድማጭ እና ተመልካቾች ተወዳጅነትን አትርፏል። ችግር ፈቺ ጉዳዮችን በመሥራት ዘመን ተሻገሪ ተግባራት አከናውኗል።
በዚህ ታታሪነቱም በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የአማራ ራዲዮ የትምህርታዊ ዘርፍ ምክትል አዘጋጅ በመሆን ሕይወቱ እስካለፈበት ጊዜ ድረስ አገልግሏል።
ጋዜጠኛ ይርጋዓለም በሥራው ታታሪ፣ ከሠራተኞች ጋር ተግባቢ፣ በኃላፊነት ዘመኑንም ሠርቶ የሚያሠራ መልካም ሰው ነበር ይሉታል ጓደኞቹ እና ባልደረቦቹ። ረጅም ሕልመኛው ጋዜጠኛ ይርጋዓለም አስማማው ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ከጋዜጠኛ ዳናዊት ሲሳይ ጋር ትዳር በመመሥረት ሁለት ወንድ ልጆችን አፈርተዋል።
ጋዜጠኛ ይርጋዓለም በማኅበራዊ ሕይወቱ ከሰው ጋር ተግባቢ ሰው አክባሪ፣ ከባልደረቦቹ ጋር መልካም ግንኙነት የነበረው፣ ሃይማኖቱን አክባሪ፣ ደግና እና ቅን ነበር። ለተቸገረ የሚደርስ፣ የታረዘን የሚያለብስ፣ የታመመ የሚጠይቅ፣ ያዘነን የሚያፅናና ልዩ መገለጫ ያለው ሰውም ነበር።
ነገር ለመኖር፣ ነገን የተሻለ ለማድረግ የሚጥረው ፣ ሕዝብን በሚያው ለማገልገል የሚያልመው፣ ብዙ መሥራት የሚያስበው ጋዜጠኛ ይርጋዓለም አስማማው ሕልሞቹን ጨርሶ ሳይይኖራቸው፣ ልጆቹን ለቁም ነገር ሳያበቃቸው ድንገት ሕመም ጎበኘው።
ሕመሙን አሸንፎ ሕልሞቹን ይኖር ዘንድ የሚያስበው ጋዜጠኛው በተለያዩ የጤና የቋማት የሕክምና ክትትል ሲያደርግ ቆይቶ ከሕመሙ ሊያገግም ባለመቻሉ በተወለደ በ38 ዓመቱ ታኅሳስ 1/2016 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም አረፈ።
ጓደኞቹ ጠዋት አብርቶ ማታ የጠፋውን ጓደኛቸውን ሲገልፁት በታላቅነት፣ በታማኝነት የሚሠራ፣ በቅንነት የሚሠራ ነው ይሉታል። ነገሮችን በሐቅ የሚናገር፣ ጓደኛን በመምክር፣ ለጥሩ ነገር በማነሳሳት፣ ጓደኞችን በመርዳት የሚታወቅ ነበርም ይሉታል። በተቋም ደረጃ ለታላላቅ ነገሮች አደራ የሚሰጥ አደራውንም በትጋት የሚወጣ ቅን እና ታታሪ ነበር ጋዜጠኛ ይርጋዓለም አስማማው።
ሩቅ አሳቢው ቅርብ አዳሪው ጋዜጠኛ ወዳጅ ዘመዶቹ፣ ጓደኞቹ በተገኙበት በባሕርዳር ጽርሀ አርያም ደብረ ሲና በዓታ ለማርያም ቤተክርስቲያን ሥርዓተ ቀብሩ ተፈፅሟል።