
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በተሃድሶ ሠልጣኞች የማጠቃለያ መርሐ ግብር ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ በሰላም እጦት ባሕርዳር ከተማ ያጣችው ብዙ ነው ብለዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች በተለይም ወጣቶች ከቱሪዝም ዘርፉ ተጠቃሚዎች ነበሩ፤ በሰላም እጦት ችግር ምክንያት ቱሪዝሙ በመቀዛቀዙ የሚገኘው ጥቅምም ተቋርጧል ነው ያሉት።
ግጭት እና የሰላም መደፍረስ ጥላ ያጠላበት የከተማዋ ብሎም የክልሉ የቱሪዝም ዘርፍ ወደ ቀደመ ቁመናው እንዲመለስ ካስፈለገ ሁሉም ለሰላም ዘብ መቆም አለበት ብለዋል።
ምክትል ከንቲባው የተሃድሶ ሥልጠናቸውን አጠናቅቀው ወደማኅበረሰቡ የተቀላቀሉ ወጣቶች ለባሕር ዳር ከተማ ሰላም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በማድረግ ሕዝብን የሚክስ፣ ራሳቸውንም ተጠቃሚ በሚያደርግ ሥራ ላይ እንዲሰማሩ ጠይቀዋል። ከተማ አሥተዳደሩ ከነዚህ ወጣቶች ጋር በጋራ እንደሚሠራም ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል።
የሰሜን ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን ባሳለፍናቸው ጦርነቶች በአማራ ክልል የሰዎች ሕይወት አልፏል፤ ከፍተኛ የኾነ የሃብት እና ንብረት ውድመት ደርሷል፤ የልጆች ትምህርት ተቋርጧል፤ የሕልውናችን መሰረት የኾነው የግብርና ሥራም ተስተጓጉሏል ብለዋል።
በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት በሰሜን ጎጃም ዞን ብቻ ከ400 ሺህ በላይ ተማሪዎች እስከ ታኀሳሥ ድረስ ወደ ትምሕርት ቤት አልተመለሱም፤ ይህ ደግሞ በተማሪዎች እና በልጆች ላይ ከፍተኛ የኾነ የሥነ ልቡና ጫና ፈጥሯል ነው ያሉት።
የሕዝብን ሰላም የሚያውኩ አካላት ሕዝብን ከዚህ በላይ መበደል የለባቸውም፤ ከዚህ የከፋም በደል የለም፤ ከድርጊታቸው ተቆጥበው ሕዝብ እፎይታን ሊያገኝ ይገባል ብለዋል።
የተሃድሶ ሥልጠናውን አጠናቅቀው ወደ ማኅበረሰቡ የተቀላቀሉ ወጣቶች በሙሉ ለአማራ ክልል ብሎም ለሀገር ሰላም፣ እድገት እና ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት ግንባር ቀደም ኾነው መሥራት ይገባቸዋል ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።
የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኮሎኔል አሸብር አሰፋ ሰላም ዋጋ አላት፤ በሰላም ውስጥ ልማት፣ ትምህርት፣ ራዕይ እና ሁሉም ነገር አለ፤ በጦርነት ውስጥ ግን የተወጠነ ህልም ሁሉ ባዶ ይኾናል ሲሉ አስገንዝበዋል።
“የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት የቆምን ለአንዲት ሀገር ኢትዮጵያ ነው፤ ሌላ አማራጭ ሀገር የለንም፤ አማራጭ ሀገር ይዘው እና የራሳቸውን ኑሮ አደላድለው እኛን ግን እርስ በእርስ እያጋጩ ለሚኖሩ አካላት ጆሮ መንሳት ያስፈልጋል” ሲሉም አስገንዝበዋል።
“አሁን ኢትዮጵያ በልጆቿ ነው እየተሰቃየች ያለችው፤ ሀገራችንን ከገጠማት ስቃይ አውጥተን ሕዝቦች ሙሉ አቅማቸውን እና ጊዜያቸውን ለልማት እንዲያውሉ ሀገር ወዳድ የኾንን ሁሉ ለሰላም መትጋት አለብን” ብለዋል።
መከላከያ ሠራዊት የሕዝብን ሰላም ውሎ ማደር አጥብቆ ይሻል፤ ለዚያም መስዋዕትነት እየከፈለም ቢኾን ቀን ከሌሊት ይሠራል ብለዋል። ሠራዊቱ ለማንም ቢኾን ጥላቻ የለውም፤ ሰላምን ለማምጣት ግን የሕግ የበላይነትን ማስከበር የግድ ይለዋል ነው ያሉት።
የተሃድሶ ሥልጠናውን ወስደው ወደ ማኅበረሰቡ የተቀላቀሉ ወጣቶችም ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ከሌሎችም የሀገርን ሰላም ከሚጠብቁ አካላት ጋር በጋራ በመኾን ለሕዝብ በሚበጅ ሥራ ላይ መጠመድ አለባቸው ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!