“ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶች ለጸጥታው ዘርፍ የማይተካ አቅም ኾነዋል” አቶ ደጀኔ ልመንህ

37

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ከአዲስ ሕይወት ሪሃብሊቴሽን እና ሪኢንተግሬሽን አሶሴሽን (አህራ) ጋር በመተባበር ከባለድርሻ አካላት ጋር በዘላቂ ሰላም ግንባታ ዙሪያ ውይይት እያካሄደ ነው።

የአማራ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ደጀኔ ልመንህ በአማራ ክልል የተከሰተው የሰላም መደፍረስ የሰው ሕይወት መጥፉቱን እና የሃብት ውድመት መድረሱን አንስተዋል። በክልሉ ላይም አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ላይ ተጽዕኖ ማድረሱን ገልጸዋል።

ለግጭቱ ሀገር በቀል የግጭት አፈታት እሴቶች መሸርሸር እና የሽምግልና ሥርዓቱ መዳከም አንዱ ምክንያት እንደኾነ አንስተዋል። ግጭቱን ለመፍታት መንግሥት እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። መንግሥት ከሚያከናውናቸው ሥራዎች ባለፈ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ድርሻም ከፍተኛ መኾኑን ነው ያነሱት።

በሰላም ግንባታ ላይ ከሚሠሩ ድርጅቶች አንዱ “አህራ” መኾኑን ያነሱት ቢሮ ኀላፊው ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ዘዴዎችን በመጠቀም እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ ለጸጥታ ዘርፉ ከፍተኛ አቅም መኾኑን አንስተዋል።
በቀጣይ ሌሎች በሰላም ግንባታ ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶችን በመጠቀም የሚታዩ አለመግባባቶችን መፍታት ይገባል ብለዋል።

የሰላም ጉዳይ በአንድ ቡድን ብቻ የሚረጋገጥ አለመኾኑን ያነሱት ቢሮ ኀላፊው ማኅበረሰቡ አጋዥ እንዲኾን አሳስበዋል። በውይይቱ ስለ ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎች እና በሀገሪቱ ስላላቸው ሚና ጥናት ቀርቧል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleባልተገባ አረዳድ የተበተኑ የቀድሞ አማራ ልዩ ኃይል አባላት መንግሥት የሚሰጣቸውን ስምሪት እና ተልዕኮ ለመቀበል ዝግጁ መኾናቸውን ተናገሩ።
Next article“አማራጭ ሀገር ይዘው፤ የራሳቸውን ኑሮ አደላድለው እኛን ግን እያጋጩ ለሚኖሩ አካላት ጆሮ መንሳት ያስፈልጋል” ኮሎኔል አሸብር አሰፋ