
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳደር ያደረገላቸውን የሰላም ጥሪ ከተቀበሉ የፋርጣ ወረዳ ዙሪያ የቀድሞ አማራ ልዩ ኃይል አባላት ጋር ውይይት ተደርጓል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ ገብቷችሁም ኾነ ሳይገባችሁ ሥርዓት አልበኝነት ውስጥ ተሰማርታችሁ የቆያችሁ አባላት ልትኖሩ እንደምትችሉ ይገመታል ብለዋል። አሁን ላይ መንግሥት ያደረገላችሁን የሰላም ጥሪ ተቀብላችሁ በሰላም መግባታችሁ እና ለውይይት መምጣታችሁ ታላቅነት ነው ብለዋል።
ዋና አሥተዳዳሪው የሕዝብን መሠረታዊ ጥያቄዎች መመለስ የሚቻለው በምክክር፣ በውይይት፣ አንድነትን በማጠናከር እና ከሌሎች ጋር በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር በመኾን ነው ብለዋል።
መንግሥት ያደረገላቸውን የሰላም ጥሪ በደስታ ተቀብለው በውይይቱ ላይ የተገኙት የቀድሞ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት በበኩላቸው መንግሥት ዳግም ጥሪ እንደሚያደርግልን ብናምንም ዘግይታችኋል ብለዋል። አሁንም ሰዓቱ ለሰላም አልረፈደም ነው ያሉት።
በሚያቀርቡት ማስረጃ መሠረት ለቆሰሉና ለተሰዉ የቀድሞ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት ካሳ እንደሚከፍል እና ጥቅማጥቅማቸውን መንግሥት እንደሚያስከብርላቸው አረጋግጠው አቅሙ እና ፍላጎቱ ያላቸውን አባላት በተለያዩ የሥራ መስኮች እንደሚፈጠርላቸው አቶ ጥላሁን ደጀኔ ገልፀዋል።
የሀገር ባለውለታ የኾነው የቀድሞ የአማራ ልዩ ኃይል ለሀገር ህልውና እና ለሕዝብ ሰላም የተዋደቀ ነው ያሉት የሠራዊቱ አባላት ባልተገባ መንገድ አላስፈላጊ ግጭት ውስጥ ቆይተናል ነው ያሉት። ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በአንድ ጉድጓድ ተቀብረናል ያሉት አባላቱ ባልተገባ አረዳድ ተበትነን ብንቆይም ከዛሬ ጀምሮ መንግሥት የሚሰጠንን ስምሪት እና ተልዕኮ ተቀብለን በታማኝነት ለመወጣት ዝግጁ ነን ብለዋል።
የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ለውይይት ከቀረቡት አባላት ጋር የተካሄዱ መድረኮች በርካታ መኾናቸውን ጠቅሰው ያለሰላም የሚኾን ነገር የለም፤ በሰላማዊ ውይይት እና ምክክር የማይፈታ ችግር አለመኖሩን የደቡብ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ መንበር ክፈተው መናገራቸውን ከደቡብ ጎንደር ዞን ኮምዩኒኬሽን መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!