
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ “ሃይማኖት ለሰላም ግንባታ” በሚል መሪ ሃሳብ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሴቶች፣ ከወጣቶች እና ከመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ጋር መክሯል።
የምክክር መድረኩን የመሩት የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ደጀኔ ልመንህ አሁን ያለው የሰላም ችግር የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን ለማስመለስ የማያስችል መኾኑን ተናግረዋል። ጥያቄዎችን ለመፍታት ሰላምን ማስቀደም እንደሚገባም አመላክተዋል። የሃይማኖት አባቶች ለሕዝብ እና ለሀገር የሚበጀውን ሰላም ማስረጽ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
ሰላም የማዕዘን ድንጋይ መኾኑንም አመላክተዋል። “የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያ የመጨረሻ ምሽግ ነው” ያሉት አቶ ደጀኔ በመከላከያ ሠራዊት ላይ የሚነዛው የተሳሳተ ወሬ ትክክል አለመኾኑን ገልጸዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ለአማራ ሕዝብ ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለ የኢትዮጵያ ሠራዊት ነው ብለዋል። “በጦርነት የተጀመረ እንጂ በጦርነት የተቋጨ ችግር የለም” ሲሉም ምክትል ኀላፊው ተናግረዋል። ይህ የዓለም እውነታ ነው፤ ከጦርነት ይልቅ ሰላምን ማስቀደም እና በውይይት ችግሮችን መፍታት ይገባል ነው ያሉት።
መንግሥት የሰላም ጥሪ እያቀረበ ነው፤ የቀረበውን ጥሪ በመቀበል ወደ ሰላም መምጣት ይገባል ብለዋል። ለዘላቂ ሰላም ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንደሚገባውም አመላክተዋል። የሃይማኖት አባቶች በየተቋሞቻቸው ስለሰላም መስበክ አለባቸው፤ የብዙኅን መገናኛ አካላት ለሕዝብ ሰላም የሚያመጣ ሚዛናዊ ሥራ መሥራት እንደሚገባቸውም አመላክተዋል።
ማኅበረሰቡም በየአካባቢው የሚንቀሳቀሰውን ወዘ ልውጥ ማጋለጥ እና ለፀጥታ ኃይሎች መጠቀም ይገባል ነው ያሉት። “እውነት እና እምነት ሁልጊዜ አይለያዩም፤ እውነት እና እምነት ከተለያዩ ግን ሰላም አይመጣም” ብለዋል። እውነትን ከውሸት፣ እምነትን ከክህደት ጋር ማቀላቀል እንደማይገባም አመላክተዋል። በአንድነት ሰላምን ማምጣት እንደሚገባም አሳሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!