“የሰላም እጦት ስለሚወልደው ችግር ጎረቤት ከኾኑ ሀገራት መረዳት እና ከእነርሱ መማር ያስፈልጋል” ኮሎኔል ተስፋዬ ኤፍሬም

62

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ” ሃይማኖት ለሰላም ግንባታ” በሚል መሪ መልእክት ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሴቶች፣ ከወጣቶች እና ከመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ጋር መክሯል።

በምክክሩ የተገኙት የባሕር ዳር እና አካባቢው ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ተወካይ ኮሎኔል ተስፋዬ ኤፍሬም የሰላም ዋጋው ሰላም ብቻ ነው፣ ሚዛኑም ሰላም ነው፣ የእኛ መውጣት እና መውረድ ለሰላም ነው ብለዋል። ሰላም ሲደፈርስ፣ ሀገር በመፍረስ አደጋ ላይ ስትወድቅ መጠገኛው ከባድ ነው ሲሉ ገልጸዋል። “የሰላም እጦት ስለሚወልደው ችግር ጎረቤት ከኾኑ ሀገራት መረዳት እና ከእነርሱ መማር ያስፈልጋል” ብለዋል።

የመከለከያ ሠራዊት በሕጉ መሰረት ለሰላም ይሠራል ሲሉም ተናግረዋል። “ተባብረን ሰላምን እናምጣው” ነው ያሉት። በጦርነት ተጀምሮ በጦርነት የመጣ ሰላም የለም፣ መጨረሻው ሰላም እና ውይይት ነውም ብለዋል።
ሰብዓዊ ውድመት ከደረሰ በኋላ ከመወያየት ውድመት ከመድረሱ በፊት መወያየትን ማስቀደም ይገባል ነው ያሉት። ሀገር የምትቆመው በመተባበር እና በመተሳሰብ ነውም ብለዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት የቆመው ለኢትዮጵያ ነው፣ቃል ኪዳን የገባውም ለኢትዮጵያ ነው፣ ለኢትዮጵያ ሰላም መኾንም ይሠራል ነው ያሉት።

የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች ለሰላም በትብብር መሥራት እንደሚገባቸውም አመላክተዋል። የራስን ተቋም እና መሪ በማዋረድ የሚመጣ ለውጥ አለመኖሩንም ገልጸዋል። ስህተቶች ካሉ መታረም አለባቸው፣ ከሕዝብ ሥነ ልቡና ጋር የማይሄዱ አካሄዶችን ግን ማረም ይገባል ሲሉ አሳስበዋል። ስለ ሰላም የመረሩ እውነቶችን መጎንጨት እና ስለ ሰላም መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል።

በውይይቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ የክልሉ መንግሥት በጥልቀት በመመርመር ችግሮችን ለመፍታት እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። የአደረጃጀት ማሻሻያ በማድረግ ወደ ሥራ መግባቱንም አስታውሰዋል። የትኛውንም ጥያቄ በሰለጠነ መንገድ መፍታት እንደሚገባም አመላክተዋል።

አሁን ላይ በተሠራው ሥራ በሁሉም አካባቢዎች አንፃራዊ ሰላም መኖሩንም ገልጸዋል። ሕዝብ ሰላሜን መልሱልኝ እያለ መኾኑን ያነሱት ምክትል ኀላፊው በተሳሳተ መንገድ ገብተው የነበሩ አካላትም ወደ ሰላም እየተመለሱ መኾናቸውንም አመላክተዋል።

“የእኛ አባቶች ብልሆች ናቸው፣ ሀገር ማቆዬትን፣ ሰላም ማምጣትን ያውቃሉ” ነው ያሉት። የሃይማኖት አባቶች የሚጠበቅባቸውን ማድረግ አለባቸው፣ ስለ እውነት ዋጋ መክፈል ያስፈልጋል፣ ሀገር የሚጸናው በእውነት ነው ብለዋል። የሃይማኖት አባቶች መደበኛ ተግባራቸው ሰላም ነው ያሉት ምክትል ኀላፊው ሰላምን የማስረፅ፣ የመስበክ እና የማስተማር ተግባራቸውን ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት።

ደም መፋሰስ እና የንጹኀን ሞት ሊበቃ እንደሚገባም አሳስበዋል። የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች የሚፈቱት በሰላማዊ ውይይት እና በጠንካራ የሥራ ባሕል መኾኑንም ገልጸዋል። ችግር ሲፈጠር ፈጥኖ አለመፍታት እና ለመፍታት አለመፈለግ የተሳሰተ አቋም መኾኑንም አንስተዋል። የሃይማኖት አባቶች ችግሮች እንዲፈቱ መሥራት ይገባቸዋልም ብለዋል። የአማራ ክልል መንግሥት ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የጸና ፍላጎት እንዳለውም ተናግረዋል። የአማራ ክልል እንዲተራመስ የሚፈልጉ አካላትን በቃችሁ ልንላቸው ይገባል ነው ያሉት።

የሰላም ሁኔታ አሳስቦን ካልሠራን መጪው ጊዜ የከፋ እንደሚኾን መገንዘብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። መንገድ ተዘግቶ ሕዝብ በረሃብ እንዲያልቅ የሚያደርግን አካሄድ መታገል ይገባል ብለዋል። ሕዝብ መልሱልኝ ያለውን ሰላም መመለስ እንደሚገባም አሳስበዋል። ሁሉም መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ እየተቀበለ ወደ ሰላም እንዲመጣም ጥሪ አቅርበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሰሜን ሸዋ ዞን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሥራን አስጀመረ፡፡
Next article“በጦርነት የተጀመረ እንጂ በጦርነት የተቋጨ ችግር የለም” አቶ ደጀኔ ልመንህ