
ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 01 /2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የ2016 ምርት ዘመን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሥራውን በአንጎለላ ጠራ ወረዳ በቡራ ቀበሌ ዛሬ አስጀምሯል። በዞን ደረጃ 24 ሺህ 646 ሔክታር መሬት በመስኖ ለማልማት እቅድ ተይዞ እየተሠራም ይገኛል፡፡
መምሪያው ዛሬ 232 ሔክታር የክላስተር መሬት ላይ ዞናዊ የመስኖ ስንዴ የዘር ማስጀመሪያ ሥራን አከናውኗል። በዞናዊ የመስኖ ስንዴ የዘር ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የዞኑ ግብርና መምሪያ ኀላፊ ታደሰ ማሙሻ እንዳሉትም ኢትዮጵያ በመሬት፣ በሰዉ ጉልበት እና በተፈጥሮ ፀጋዎች የታደለች ናት፡፡
ይሁን እንጅ የድህነት ታሪክ ግን አብሯት እየተጓዘ በመኾኑ ፈጥኖ ብዙ በማምረት ታሪክን መቀየር እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ አሁን እየታየ ያለውን የዋጋ ንረት ለመከላከልም ብቸኛው መፍትሄ ማምረት እንደኾነ ተናግረዋል፡፡
ሀገርን ከችግር የማላቀቅ አንድ የእቅድ አካል ለኾነው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል፡፡ ለዚህም ሥራውን በዞን ደረጃ ትኩረት ሰጥቶ ለመምራት ዛሬ ሥራው በይፋ መጀመሩንም ገልጸዋል።
የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሥራው በ23 ወረዳዎች ተግባራዊ እንደሚኾንም በማስጀመሪያ መርሐግብሩ ላይ ተገልጿል፡፡ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም 2 ሺህ 400 ሄክታር በላይ ማሳ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት መሸፈኑን የዞኑ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን መምሪያ ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!