
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ “ሃይማኖት ለሰላም ግንባታ” በሚል መሪ ሃሳብ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሴቶች፣ ከወጣቶች እና ከመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ጋር መክሯል።
በምክክሩ የተገኙት የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደስዬ ደጀን ሰላም በፍላጎት ብቻ የሚሳካ አይደለም፤ ለሰላም መትጋት ይገባናል ነው ያሉት። “በአማራ ክልል ያለው የሰላም እጦት መጀመሪያ የሚጎዳው የክልሉን ሕዝብ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
ኮሚሽነሩ በአማራ ክልል በርካታ ተቋማት ችግር ውስጥ ገብተዋል፤ ተዘርፈዋል፤ አደጋ ደርሶባቸዋል ነው ያሉት። ችግሩ የሚጎዳው የአማራን እናቶች፣ ከፍ ሲልም የአማራን ሕዝብ ነው ብለዋል። የሃይማኖት አባቶች ወጣቶችን መምክር እና ወደ ጥፋት ሲያመሩም መገሰጽ አለባቸው ያሉት ኮሚሽነሩ ካልተገባ አካሄድ መቆጠብ እንደሚገባ አሳስበዋል። ጦርነት የአማራን ሕዝብ በእጅጉ ይጎዳል፣ ከጦርነት በፊት ያሉ አማራጮችን መጠቀም ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ምርት በሚሰበሰብበት ወቅት ግጭት መፍጠር ለየትኛውም ችግር መፍትሔ አይኾንም ብለዋል። መንገድ ዝጋ በማለት፣ በትምህርት ቤቶች ቦንብ በመጣል፣ እና መሰል ኀላፊነት የጎደላቸው ድርጊቶችን በመፈጸም የሚመጣ መፍትሔ አለመኖሩንም ገልጸዋል።
በመገዳደል የሚመጣ መፍትሔ የለም፤ መጠቅለል እና መፈረጅ ትክክል አይደለም፤ በተሳሰተ መረጃ አማካኝነት ሁሉንም መፈረጅ የተገባ አለመኾኑንም አሳስበዋል። በመከላከያ ሠራዊት እና በሌሎች የጸጥታ ተቋማት ላይ የሚስተዋለው ያልተገባ ዘመቻ የተሳሳተ መኾኑንም ገልጸዋል። መከላከያ ሠራዊት መስዋዕትነት እየከፈለ ያለው የሕዝብን ሰላም ለማረጋገጥ እንጂ ሌላ ዓላማ እና ፍላጎት ኖሮት አይደለም ብለዋል። ሠራዊቱን ባልተገባ መንገድ መፈረጅ ትክክለኛ አካሄድ አለመኾኑንም አመላክተዋል።
አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ለጥፋት የቆሙ አካላትን አይዟችሁ እያሉ ማበጣበጥ እና ሕዝብ ማወክ ሊቆም ይገባልም ብለዋል። ሰላም ለሁላችን እንደሚያስፈልግ ሁሉ ሰላምን ለማምጣትም ሁላችንም መትጋት አለብን ብለዋል። ወደ ውስጣችን እንመልከት፣ የራሳችን ችግር ራሳችን እንፍታ ነው ያሉት።
ፖሊስ በክልሉ የተሟላ ሰላም ለማምጣት እየሠራ መኾኑን ያነሱት ኮሚሽነሩ በሕግ ማስከበር ሥራው ያልተገባ አካሄድ ካለ እየተገመገመ ይስተካከላል፤ ለዚህም ሁሉም የፖሊስ አካል ትብብር ሊያደርግ ይገባልም ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!