
ሰቆጣ: ታኅሳሥ 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ተማሪ ብስራት ተፈራ የአምደወርቅ አንደኛ እና መለስተኛ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ ተማሪው ለክልል አቀፍ ፈተና በቂ ዝግጅት እያደረገ መኾኑን ተናግሯል፡፡ አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በአንድ የትምህርት ዓይነት ብዙ ይዘቶችን የሚያነሳ እና የተሻለ ዕውቀት የሚሰጥ ነው ሲል ገልጿል።
ተማሪ ሊዲያ ዘላለም በዚሁ ትምህርተት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ ናት። አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት አገርን የሚያሳውቅ፣ ተማሪዎችም በሥነምግባር የሚቀርጽ ነው ብላለች፡፡ መምህራንም የቀደመውን ከአዲሱ ጋር እያስማሙ ስለሚያስተምሩ በክልላዊ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እየጣረች መኾኑን አንስታለች፡፡ የትምህርት ቤቱ የዜግነት ትምህርት መምህር ምስጋናው ተረፈ የትምህርት ጥራት እንዲጠበቅ ለማድረግ የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
የአምደወርቅ አንደኛ እና መለስተኛ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር ሻንበል ቢምር ትምህርት ቤቱ በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት አጋጥሞት እንደነበር አንስተዋል፡፡ ከመንግሥት እና ከረጅ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ወደነበረበት ደረጃ ለመመለስ ጥረት መደረጉንም አንስተዋል፡፡ የትምህርት ቤቱ የተማሪ የቅበላ አቅሙንም በእጥፍ በማሳደግ ከ2 ሺህ 850 በላይ ተማሪዎች በሁለት ፈረቃ እያስተማሩ መኾኑንም ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቱ ለትምህርት ጥራት ከፍተኛ ዋጋ በመሥጠት ተማሪዎች ከመሰረቱ ጀምረው በጥራት እንዲያልፉ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ ርእሰ መምህሩ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የተዘጋጀውን መጽሐፍ ለተማሪዎች በቡድን እያደረስን ነው ብለዋል፡፡ የጅኩፕ በጀት ባለመለቀቁ የመማር ማስተማር ሥራውን የሚያግዙ ቁሳቁሶችን ለመግዛት መቸገራቸውን አንስተዋል፡፡
የድሃና ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ተወካይ ኀላፊ ደሳለኝ ካሳው በወረዳው አጸደ ሕጻናትን ጨምሮ ከ36 ሺህ 690 በላይ ተማሪዎች በመማር ላይ እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ ወረዳው የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከምንግዜውም በላይ ትኩረት ሠጥቶ እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ አቶ ደሳለኝ በቀጣይም ይህንን ሥራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡
ወረዳው የመማር ማስተማር ሥራውን ለማሻሻል ባለው በጀት ሥልጠና እና ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡ ተወካይ የጅኩፕ በጀት በክልል ደረጃ በተሰጠን አቅጣጫ መሰረት በዘንድሮው ዓመት እንደማይለቀቅ ተነግሮናል፤ እኛም ይህንን አሳውቀናል ያሉት ተወካይ ኃላፊው በተማሪ ቁጥር የሚሰጠው በጀት ግን ተለቅቆልን ለሁሉም ትምህርት ቤቶች አከፋፍለናል ሲሉ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!