“ትውልድ ከእውነት እና ከምክንያት በሸሸ ቁጥር ሀገር መመለሻ ወደሌለው አዘቅት ትገባለች” የአማራ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ

58

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 1/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ “ሃይማኖት ለሰላም ግንባታ” በሚል መሪ መልዕክት ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሴቶች፣ ከወጣቶች እና ከመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ጋር እየመከረ ነው።

በምክክር መድረኩ መልእክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ ክልሉ ባጋጠውም የሰላም መናጋት ምክንያት ከፈተኛ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ማስተናገዱን ገልጸዋል።

የአማራ ሕዝብ በሀገረ መንግሥት ግንብታ ታሪክ ጉልህ ስፍራ ያለው በአብሮነት እና በትብብር ሀገር ያጸና፣ ሕግ የቀረፀ፣ ፍርድ ጎደለ ደሀ ተበደለ የሚል፣ የሕግ የበላይነት መኖርን የሚያምን፣ ሕግ መንግሥትን ከቤተ እመነት ጋር አስተሳሳስሮ የያዘ መኾኑን ገልፀዋል።

የአማራ ሕዝብ ምኞት እና ፍላጎት በትንንሽ ሀሳቦች የሚያንስ ሳይኾን፣ ከዘመን ጋር አብሮ የሚዘምን፣ ተራማጅ እና አዳዲስ ሃሳቦችን አመንጪ፣ ለአብሮነት እጁ የተዘረጋ፣ የእውነተኛ ኢትዮጵያዊነት የቃል ኪዳን መሠረቱ የማይናወጥ ፅኑ ሕዝብ ነው ብለዋል። የአማራ ሕዝብ ተለይተው ያደሩ ጥያቄዎች በሰላም እና በፍትሕ እንዲፈቱለት ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር ኾኖ የሚታገል ጨዋ ሕዝብ መኾኑንም አመላክተዋል።

የአማራ ሕዝብ ታላቅ ሕዝብ ነው የምንለው በብዛቱ እና በቁዳ ስፋቱ አይደለም ያሉት ምክትል ኀላፊው ትናንትን ከዛሬ፣ ዛሬን ከነገ ጋር አሰናስሎ ችግሮችን በጥበብ የሚፈታ በመኾኑ ነው ብለዋል። ዋጋ የከፈለባትን ሀገሩን የሚጠብቅ፣ እየሞተ እና እየተገፋም ቢኾን ሀገሩን የሚወድ፣ ችግሮችን በስከነት እና በሕግ አግባብ እንዲፈቱለት የሚተጋ ሥልጡን ሕዝብ መኾኑ የታላቅነት መገለጫዎቹ መኾናቸውን አንስተዋል።

ለዘመናት የኖረው ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ እሴቱ ሚዛን ጠብቆ እንዲኖር በጋራ መሥራት ይገባል ነው ያሉት። ከእውነት ጋር መጋፈጥ ያልቻለ ትውልድ ለሀገር የማይኾን ደካማ እና ተቅበዝባዥ እንደሚኾን ገልጸዋል። ትውልድ ከእውነት እና ከምክንያት፣ ከአባቶቹ ቃል፣ ከባሕል እና ከእምነቱ፣ ከሀገሩ እና ከታሪኩ እየሸሸ በሄደ ቁጥር ሀገር መመለሻ ወደሌለው አዘቅት ትገባለች ነው ያሉት።

ትወልዱ ብኩን እንዳይኾን የሚመክሩ እና የሚገስጹ አባቶች ያስፈልጉታልም ብለዋል። ከዘረኝነት የጸዳ፣ ለሀገሩ ተስፋ የሚኾን ትውልድ እንዲኖር አባቶች ኀላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ነው ያሉት። አባቶች የሚፈስሰውን ደም የሚያስቆሙበት ጊዜው አሁን መኾኑንም ገልጸዋል። ዘመኑን ባልዋጀ ቅስቀሳ እና በጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ሀገር ያፈርስ ይኾናል እንጂ የሚያሳካው ግብ የለውም ነው ያሉት።

ምክትል ቢሮ ኀላፊው ከእውነት ጋር መቆም ዋጋ የሚያስከፍም ቢኾንም የሃይማኖት አባቶች እውነታውን እያስተላለፉ ሰላም እንዲመጣ እንዲሠሩም ጠይቀዋል። መፍትሔው ከእጃችን ላይ መኾኑን አውቀን በትጋት ልንሠራ ይገባልም ብለዋል። ችግሮችን በሰከነ መንገድ በውይይት እና በንግግር መፍታት ይገባል ነው ያሉት።

ሁሉም የሰላም አምባሳደር በመኾን የተጀመረውን ሰላም ማስጠበቅ አለበትም ብለዋል። የክልሉ መንግሥት የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እየሠራ መኾኑንም አመላክተዋል። ከዚህ በላይ በዚህ ሁኔታ መቀጠል ራስን በጨለማ ውስጥ እንደማኖር ይቆጠራል ያሉት ምክትል ኀላፊው ችግሮችን በውይይት እና በሰላም መፍታት ይገባናልም ብለዋል።

በምክክር መድረኩ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደስዬ ደጀን፣ የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ደጀኔ ልመንህ፣ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ29 ሺህ ሄክታር በላይ የበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት እየሠራ መኾኑን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አስታወቀ፡፡
Next articleየትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን የድሃና ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።