
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከ29 ሺህ ሄክታር በላይ የበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት እተሠራ መኾኑን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አስታውቋል። የመምሪያው ኀላፊ ንጉሤ ማለደ እንደገለጹት ዞኑ ለበጋ መስኖ ልማት ትኩረት ሰጥቶ እየተሠራ ነው።
አቶ ንጉሴ በ2016 ዓ.ም የመስኖ ልማት ወቅት ከ29 ሺህ 700 ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ለመሸፈን እየተሠራ ነው ብለዋል። ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ምክክር በማድረግ የጋራ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ ከዞን እስከ መስኖ ተጠቃሚዎች ድረስ የመስኖ ንቅናቄ በማድረግ ከአርሶ አደሮች ጋር መግባባት ላይ ስለመደረሱም አንስተዋል፡፡
እስካሁን ድረስ በዞኑ 20 ሺህ ሄክታር መሬት ለመስኖ ልማት መለየቱን የተናገሩት ኃላፊው ከ13 ሺህ ሄክታር በላይዩ መሬት ታርሷል፤ ከ7 ሺህ ሄክታር በላዩ ደግሞ በዘር ተሸፍኗል ተብሏል፡፡ ባለፈው ዓመት ከነበረው የግብዓት አቅርቦት እጥረት ትምህርት በመወሰድ ችግሮችን የሚፈቱ ሥራዎችን መሥራታቸውንም ገልጸዋል፡፡
በዞኑ ሠፊ መሬት የሚሸፍነው የሰራባ የመስኖ ፕሮጄክትን በሙሉ አቅም ለመጠቀም እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የመስኖ ፕሮጄክቱ 4 ሺህ ሄክታር መሬት እንደሚያለማም ገልጸዋል፡፡ የመስኖ ፕሮጄክቱ የካናል ጠረጋ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ ጠረጋው በአስቸኳይ እንዲጠናቀቅ በማኅበረሰብ ተሳትፎ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ በሰራባ መስኖ ፕሮጄክት የሚታየው ችግር እንዲፈታ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መነጋገራቸውንም ገልጸዋል፡፡
መስኖን ለመጠቀም ተጨማሪ ሥራዎች እና ቴክኖሎጂን መጠቀም እንደሚጠይቅ የተናገሩት ኀላፊው በዞኑ ከ100 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በመስኖ መልማት እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡ በዞኑ ያለውን ሙሉ አቅም ለመጠቀም ግን ትልልቅ ግድቦች መገደብ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች፣ የግብርና ምርምር ተቋማት እና ሌሎች ድጋፍ ማድረግ የሚችሉ ከኾነ በቴክኖሎጂ እጥረት ምክንያት ጥቅም ላይ ያልዋሉ ቦታዎች በመስኖ መልማት ይችላሉ ብለዋል፡፡፡ “የዳቦ ጥያቄዎችን መመለስ ግድ ይላል” ያሉት ኀላፊው የግብርና መሪዎች እና ባለሙያዎች ሥራ ላይ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!