“መንግሥት አስቸኳይ ድጋፍ ለሚስያስፈልጋቸው ወገኖች የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሠራ ነው” የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን

58

በአማራ ክልል በተከሰተው ድርቅ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖች ለችግር መጋለጣቸውን በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በተለይም በተከዜ ተፋሰስ የሚገኙ ወገኖች ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን በተደጋጋሚ ተነስቷል፡፡

በክልሉ የተከሰተው ድርቅ ባስከተለው ረሃብ ወገኖች መሞታቸውን በጥናት ስለመረጋገጡም አሚኮ ዲጅታል ሚዲያ ለተከታዮቹ አድርሷል። በክልሉ በድርቅ የተጎዱ ወገኖችም አስቸኳይ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡

የአማራ ክልል መንግሥትም በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ሕይዎት ለመታደግ ልዩ ትኩረት ሰጥቼ እየሠራሁ ነው ብሏል፡፡ መንግሥት ብቻውን ሊቋቋመው የማይችል በመኾኑ ረጂ ድርጅቶች፣ ባለሃብቶች፣ ነጋዴዎች እና የተሻለ ያመረቱ አርሶ አደሮች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ መቅረቡ ይታወሳል፡፡

በመላ ሀገሪቱ የሰብዓዊ ድጋፍን የሚያደርሰው የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽንም አስቸኳይ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች የሰብዓዊ ድጋፍ እያደረኩ ነው ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አታለለ አቡሃይ ኮሚሽኑ ለዜጎች የሰበዓዊ ድጋፍ መስጠት ዋነኛ ድርሻው መኾኑን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ጊዜያት የዓለም የምግብ ድርጅት እና ሌሎች መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት በልዩ ልዩ ምክንያቶች እርዳታቸውን አቋርጠው እንደነበር ያስታወሱት ባለሙያው መንግሥት በመካከል የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት ለወገኖቹ እርዳታ ሲሰጥ መቆየቱንም አስታውቀዋል፡፡

መንግሥት ከመጠባበቂያ የምግብ ክምችቱ በማውጣት ለ7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ወገኖች እርዳታ ሲሰጥ መቆየቱንም አመላክተዋል፡፡ እርዳታው የአይነት እና የገንዘብ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የተደረገው ድጋፍ በገንዘብ ሲተመን 7 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር እንደሚያወጣም ተናግረዋል፡፡

በልዩ ልዩ ምክንያቶች እርዳታቸውን አቁመው የነበሩ አጋር አካላት ከመንግሥት ጋር በተደረሰው ስምምነት መሠረት ወደ መደበኛ ሥራቸው ተመልሰው እርዳታ ለመስጠት ከኮሚሽኑ ጋር ሥራ መጀመራቸውንም አስታውቀዋል፡፡

አጋር አካላቱ ከኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ጋር በመኾን የቅድሚያ ቅድሚያ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ድጋፍ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል፡፡ በጎርፍ፣ በድርቅ እና በሰው ሠራሽ ችግሮች ውስጥ ለወደቁ ወገኖች የቅድሚያ ቅድሚያ ተሰጥቶ ድጋፍ እንደሚደረግም አመላክተዋል፡፡

እንደ ሀገር ትክክለኛ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብለው ለተለዩ 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ወገኖች እርዳታው ይደርሳልም ብለዋል፡፡ 867 ሺህ ኩንታል ምግብ ነክ እርዳታ እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡ ከዓለም ባንክ የተገኘ 560 ሚሊዮን ብርም ለተጎጂ ወገኖች ይከፋፈላል ነው የተባለው፡፡

በአጠቃላይ 8 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት እርዳታ ለወገኖች ይቀርባልም ተብሏል፡፡

በሁሉም ክልሎች የቅድሚያ ቅድያ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ድጋፉ ይደረጋልም ብለዋል፡፡

የኮሚሽኑ የዕለት ደራሽ እርዳታ ጫኝ መኪኖች በመጫን ላይ መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡ እርዳታው በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚደርስም ገልጸዋል፡፡

አጋር አካላት ወደ መደበኛ ሥራቸው በመመለሳቸው ለሁሉም ተረጂዎች መድረስ ይቻላልም ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል እና በሌሎች ክልሎች በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ይደረጋልም ነው ያሉት፡፡

“መንግሥት አስቸኳይ ድጋፍ ለሚስያስፈልጋቸው ወገኖች የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሠራ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

ከሰብዓዊ ድጋፍ ባለፈ ሌሎች ድጋፎች እንዲቀርቡ ኮሚሽኑ የማስተባበር ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን በሚመሩት የአደጋ ስጋት አመራር ምክር ቤት በተደጋጋሚ ድርቅ የሚያጠቃቸውን አካባቢዎች የአደጋ ስጋት ቅነሳ እንዲሠራ አቅጣጫ መቀመጡንም ተናግረዋል፡፡

ዜጎች ሁልጊዜ ተረጂ ኾነው እንዳይቀጥሉ፣ ራሳቸውን እንዲችሉ እና ከድርቅ ጉዳት ፈጥነው እንዲወጡ የማድረግ ተጨባጭ የኾነ ሥራ እንዲሠራ አቅጣጫ ተቀምጧል ነው የተባለው፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በየድርሻቸው የአደጋ ስጋት ቅነሳ ላይ በትኩረት እንዲሠሩም አቅጣጫ ተቀምጦላቸዋል ነው ያሉት፡፡

ችግሩ ከመድረሱ አስቀድሞ ዜጎች ለአደጋ ተጋላጭ የሚያደርጓቸውን ጉዳዮች መቀነስ እና ተጋላጭ እንዳይኾኑ በሚያደርጓቸው ተግባራት ላይ ትኩረት ይደረጋልም ብለዋል፡፡

በድርቅ እና ጎርፍ አደጋ ሊጠቁ የሚችሉ አካባቢዎች ተለይተው እየተጠኑ እንደኾነ የተናገሩት ባለሙያው ቅድሚያ በመሥራት አደጋውን የማስቆም ሥራ በትኩረት ይሠራበታል ነው ያሉት፡፡

ሁሉም ዜጎች ለአደጋ ተጋላጭ የማይኾኑበትን ሥራ መሥራት ይገባልም ብለዋል፡፡

በድርቅ አደጋ የተጠቁ የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦቱ ልዩ ትኩረት የሚሰጣቸው መኾናቸው ተመላከቷል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በበጎ ፈቃድ መርሃ ግብር የተሠሩ ቤቶችን እና ትምህርት ቤት ገንብቶ አስረከበ።
Next articleበኩር ጋዜጣ ታኅሳስ 01/2016 ዓ.ም ዕትም