
ጎንደር: ኅዳር 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የተረጋጋ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች የመንገድ መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት እና የሥራ እድል ለመፍጠር እንደሚሠራ የክልሉ መንገድ ቢሮ ገልጿል።
ቢሮው የባለፋት አራት ወራት አፈጻጸም እና የቀጣይ እቅድን በጎንደር ከተማ ገምግሟል።
በክልሉ ተከስቶ የነበረው የሰላም መደፍረስ ወደ አንጻራዊ ሰላም እየተመለሰ በመኾኑ በበጀት ዓመቱ የታቀዱ ሥራዎችን ለመፈጸም ይሠራል ተብሏል።
አሁን ላይ የክልሉ የመንገድ ሽፋን 31 ሺህ 300 ኪሎ ሜትር በላይ ሲኾን እስከ 2022 ዓ.ም ድረስ ሽፋኑን 51ሺህ 600 ኪሎ ሜትር በላይ ለመፈጸም አቅዶ እየሠራ መኾኑን ገልጿል ቢሮው።
በ2016 በጀት ዓመት 516 ፕሮጀክቶች በክልሉ ለመሥራት የታቀደ ሲኾን የታቀዱ እቅዶችን ለማሳካት በትኩረት እንደሚሠራ የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ኀላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ.ር) ገልጸዋል።
በዚህ ዓመት 92 የተለያዩ መጠን ያላቸው ድልድዮች ለመሥራት ብለዋል። 62 የሚኾኑት በዚህ ዓመት ተጠናቅቀው ወደ ሥራ እንዲገቡ እንደሚሠራ እና በተጨማሪም 217 የስትራክቸር ሥራዎች ይሠራል ነው ያሉት።
ለፕሮጀክቶችም 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በክልሉ መንግሥት ተመድቧል፤ በፌዴራል መንግሥት በኩል 890 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር እና ከኅብረተሰቡ ተሳትፎም 800 ሚሊዮን ብር በጥቅሉ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ሥራ ላይ እንደሚውል የቢሮ ኀላፊው ገልጸዋል።
በክልሉ የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ በመንገድ ሥራዎች ላይ መስተጓጎል የፈጠረ ቢኾንም አንጻራዊ ሰላም ባሉበት አካባቢዎች ላይ 980 ኪሎ ሜትር የመንገድ ጥገና ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።
በዚሁ ሳቢያ 52 የፌዴራል አስፓልት ፕሮጀክቶች በክልሉ ውስጥ ሥራ ላይ የነበሩ ቢኾንም 20 ፕሮጀክቶች ብቻ ናቸው ተረጋግተው መሥራት የቻሉት ነው ያሉት ኀላፊው። በቀጣይ ሁሉም ወደ ሥራ እንዲገቡ ይሠራል ብለዋል።
ከታኅሣሥ 1/2016 ዓ.ም ጀምሮም በሕዝብ የሚነሱ የመልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች እቅዱን ለማሳካት እንደሚሠራ አስገንዝበዋል።
በሥራውም ለ22 ሺህ ወጣቶች የሥራ እድል ይፈጠራል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ዳንኤል ወርቄ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!