ቡና ባንክ ከ1ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ያልተጣራ ትርፍ ማግኘቱን ገለጸ።

44

አዲስ አበባ: ኅዳር 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ቡና ባንክ የ14ኛ መደበኛ የጠቅላላ የባለ አክሲዮኖች ጉባዔን እያካሔደ ነው።

የባንኩን ዓመታዊ ሪፖርት ያቀረቡት የቡና ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አምባሳደር ዓለማየሁ ሰውአገኝ ከተመሰረተ 14 ዓመት የሞላው ቡና ባንክ ጠንካራ እና ተወዳዳሪ ኾኖ ቀጥሏል ብለዋል።

ሀገር አቀፍ አለመረጋጋት እና ዓለም አቀፍ ጫና ለባንኩ እድገት እና ሥራ እንቅፋት መኾኑን ጠቅሰዋል።

የተቀማጭ ገንዘብ መጠን በዓመቱ 9 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ማድረስ የቻለው ባንኩ ጠቅላላ ተቀማጩንም ወደ 36 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ማድረስ እንደቻለ ነው የተገለጸው።

እንደቦርድ ሊቀመንበሩ ገለፃ ባንኩ 11 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ብድር መስጠትም ችሏል።

የብድር አሰጣጡ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ34 ነጥብ 5 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

የመክፈያ ጊዜ ያለፈባቸው ብድሮች መጠን 3 ነጥብ 48 በመቶ ብቻ እንደኾነም አስረድተዋል።

የውጭ ምንዛሬን በተመለከተ በቀረበው ሪፖርት ላይም የ175 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መሠብሠብ ችሏል።

በዓመቱ ያለውን ጠቅላላ ሀብት 12 በመቶ በማሳደግ 46 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ማድረሱን ተናግረዋል።

ባንኩ ጠቅላላ ያለውን ካፒታል 4 ነጥብ 28 ቢሊዮን ብር ማድረሱን የቦርድ ሊቀመንበሩ ገልጸዋል።

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት መጠን 1 ነጥብ 63 ቢሊዮን ብር መድረሱም ተብራርቷል።

በዚህ ዓመት ባንኩ የ6 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱንም ነው የገለጸው።

የ1 ነጥብ 36 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ እንዳለውም ነው የተነገረው።

የባንኩ የተጣራ ትርፍ 989 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ገደማ ሲኾን ከዚህ ውስጥ የ745 ሚሊዮን ብር ገደማ የሚኾነውን ለባለአክሲዎኖች የትርፍ ክፍፍል እንዲውል ወስኗል።

ባንኩ አንድ ሚሊዮን 90 ሺህ ገደማ አዳዲስ ደንበኛ በዓመቱ አፍርቻለሁ ያለ ሲኾን የጠቅላላ ደንበኛ ቁጥርን 3 ሚሊዮን 50 ሺህ በላይ ማድረሱን አሳውቋል።

በበጀት ዓመቱ 122 ቅርንጫፎችን በመክፈት የቅርንጫፍ መጠኑን 465 አድርሷል።

ከእነዚህ ውስጥ 35 በመቶ የሚኾኑት በአዲስ አበባ የሚገኙ ናቸው ነው የተባለው።

ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው።
Next articleበክልሉ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር በመንገድ ሥራ ላይ ችግር መፍጠሩን የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ አስታወቀ።