ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው።

44

ባሕር ዳር: ኅዳር 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ዘላቂ ሰላምን ማስፈን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው።

ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከደብረ ብርሃን ነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት የገጠመንን የሰላም እጦት ችግር በመነጋገር መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል። በተደጋጋሚ በሚከሰቱ ግጭቶች በክልሉ ላይ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት እየደረሰ መኾኑንም ነው ያስገነዘቡት።

ቀደም ሲል የሰሜኑ ጦርነት የሰው ሕይወት መጥፋት እንዲሁም የሀብትና ንብረት መውደም ማስከተሉን ገልጸዋል። የደረሰውን ውድመት መልሶ ለመተካት ጥረት እየተደረገ ባለበት ወቅት ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ በተከሰተው ግጭት በክልሉ ሕዝብ ላይ ዳግም የከፋ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማን የኢንቨስትመንት ተመራጭነት አጠናክሮ ለማስቀጠል ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባም ነው ርእሰ መሥተዳድሩ የተናገሩት።

የተጀመሩና ገና ለማስጀመር በእቅድ ላይ የነበሩ የልማትና መልካም አሥተዳደር ሥራዎች እንዲቆሙ በማድረግ የክልሉ እድገት እንዲገታ አድርጎታል ብለዋል። ይሁን እንጂ መንግሥት የመከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኃይሎችን በማሰማራት በወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም ማስፈን መቻሉን አስረድተዋል።

የደብረ ብርሃንና አካባቢው ሕዝብም በየጊዜው የሚፈጠሩ ግጭቶች ክልሉን ወደ ድህነት አረንቋ የሚወስዱ መሆናቸውን በመገንዘብ ዘላቂን ሰላምን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት መሥራት አለበት ብለዋል።

መንግሥት እና ሕዝብ በጋራ ዘላቂ ሰላምን ማስፈን ከቻሉ የከተማዋን በኢንቨስትመንት ተመራጭነት አጠናክሮ ማስቀጠል ይቻላል ብለዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብእሸት ከተማዋ በኮማንድ ፖስት እንድትመራ ከኾነ ወዲህ የጸጥታ ሁኔታው በእጅጉ ተሻሽሏል ብለዋል።

በተገኘው አንጻራዊ ሰላምም ባለሀብቶች 80 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን በማቅረብ ምልመላ፣ መረጣና ፈቃድ የመስጠት ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።

ከቀረቡት ውስጥም መስፈርቱን ላሟሉ 36 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መሬት እንደተሰጣቸው አስታውቀዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ ነዋሪዎችም ዘላቂ ሰላምን ለማረጋጥ በየደረጃው ውይይቶች ሊደረጉ ይገባል ነው ያሉት።

ያጋጠመው የሰላም እጦትም ሕይወታቸውን አስቸጋሪ እንዳደረገባቸውም ነዋሪዎቹ በመድረኩ አንስተዋል።

በውይይቱ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የአማራ ክልል ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)፣ የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ዋና አዛዥና የማዕከላዊ ሸዋ ኮማድ ፖስት ሰብሰቢ ሌተናል ጀነራል ሹማ አብደታ እና ሌሎች መሪዎች በመድረኩ ተገኝተዋል፡፡

የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች፣ ነጋዴዎችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች በውይይቱ ተሳትፈዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የወንጀል መከላከልና የምርመራ ሥራዎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እየተከናወኑ ነው” ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ
Next articleቡና ባንክ ከ1ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ያልተጣራ ትርፍ ማግኘቱን ገለጸ።