
ባሕር ዳር: ኅዳር 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የወንጀል መከላከልና የምርመራ ሥራዎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና በላቀ ሙያዊ ብቃት እየተከናወኑ መኾኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ ገለጹ።
በኢትዮጵያ የ’ሪፎርም’ ሥራዎች ከተደረገባቸው ተቋማት መካከል የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። ተቋማቱም በሀገር እና ሕዝብ ላይ የሚቃጡ ወንጀሎችን ቀድሞ መከላከልና ተፈጽመውም ሲገኙ በላቀ የምርመራ ብቃት አጣርቶ ለሕግ የማቅረብ ሥራ እያከናወኑ ይገኛሉ። በዚህም የሀገርንና የሕዝብን ደኅንነት በአስተማማኝነት መልኩ መጠበቅ የሚያስችል አቅም መፈጠሩን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ የፖሊስ የመጀመሪያ ሥራ መረጃ መር የኅብረተሰብ አገልግሎት ላይ የተመሰረተ የወንጀል መከላከል ተግባር በመኾኑ በዚሁ መሰረት እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በዜጎች እና በሀገር ላይ የሚቃጡ ወንጀሎችን በመከላከልና የምርመራ ሥራዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በላቀ ሙያዊ ብቃት እየተከናወኑ መኾኑን አረጋግጠዋል።
የዜጎችን ደኅንነት በአስተማማኝ መልኩ በመጠበቅ እየተደረገ ባለው ጥረትም የኅብረተሰቡ ተሳተፎ የላቀ ሚና እንዳለው ጠቅሰው ይሄው ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል ብለዋል።
የፖሊስ የወንጀል መከላከልና የምርመራ ሥራዎች ብቃት ባለው የሰው ኃይል እና ዘመኑ ባፈራቸው ቴክኖሎጂዎች እየተከናወኑ መኾኑን ጠቅሰው በቀጣይም በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መኾኑን ተናግረዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው የሀገሪቱን ብሎም የቀጣናውን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥም ከኢንተርፖል እንዲሁም ጎረቤት ሀገራት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መኾኑን ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!