“ወንድማማችነት ከፖለቲካ ርእዮትም፤ ከሃሳብ ልዩነትም በላይ ነው” ምሁራን 

94

ባሕር ዳር: ኅዳር 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በጃፓን የሶፊያ ዩኒቨርሲቲ ኢንስቲትዩት የፖለተካል ሳይንስ ተመራማሪ ጣሊያናዊው ፕሮፌሰር አንቶኒዮ ማሪያ ባጊዮ ወንድማማችነትን “የተዘነጋው ፖለቲካዊ መርሕ” ሲሉ ይጠሩታል፡፡ በባሕል፣ በሃይማኖት እና በምጣኔ ሃብታዊ ግንኙነት ውስጥ ትርጉም ያለው ወንድማማችነት በፖለቲካ ርእዮተ ዓለም ዘንድ መዘንጋቱ በፍቅር የሚፈቱ ቅራኔዎች ጦር አማዝዘው ወደ ደም አፋሳሽ እልቂት ሲያመሩ እናያለን ይላሉ፡፡

 

ፕሮፌሰሩ አያይዘውም የትኛውም ቅራኔ በጦርነት አልቆ አያውቅም፤ ከብዙ መላላጥ እና አስከፊ መሥዋዕትነት በኋላ ሁሉም ቅራኔዎች የሚፈቱት በእርቅ ነው ይላሉ፡፡ በእርግጥም የፕሮፌሰሩ ሃሳብ በዓለም የጦርነት ታሪክ መነጸር ከታየ ፍጹም እውነታ መኾኑን ደጋግመን አይተናል፡፡ አይደለም የጋራ እጣ ፋንታቸው በአንድ የተገመደ የአንድ ሀገር ዜጎች ውስጣዊ ግጭት ድንበር አቋርጠው እና ባሕር ተሻግረው ጦርነት ውስጥ የገቡ የተለያዩ ሀገራት እንኳን ደም አፋሳሽ ጦርነቶቻቸው የተቋጩት በእርቀ ሰላም ነበር፡፡

 

በመኾኑም ፕሮፌሰር አንቶኒዮ ማሪያ ባጊዮ በፖለቲካ ርእዮተ ዓለም ውስጥ ከሁሉም ነገር በላይ የወንድማማችነት መርሕን ማስቀደም ተገቢ ነው ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ ወንድማማችነት ተፈጥሯዊ የኾነውን የሃሳብ ልዩነት ተከትሎ የሚፈጠሩ ቅራኔዎችን በሰከነ፣ በሠለጠነ እና ዘላቂ በኾነ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል ፖለቲካዊ መርሕ ስለመኾኑ ደጋግመው ያነሳሉ፡፡ ምንም እንኳን ግጭት በሰው ልጅ የዘመናት ኑባሬ ታሪክ ውስጥ ተፈጥሯዊ ቢኾንም ከሁሉም በላይ መቅደም ያለበት ግን የወንድማማችነት መርሕ ሊኾን እንደሚገባ ያስገነዝባሉ፡፡

 

በ16ኛው እና 17ኛው ምዕተ ዓመት ገደማ ብርቱ ጠባሳ ጥለው ካለፉት ግጭቶች እና ጦርነቶች ማግስት ጀምሮ በመላው ዓለም ባሉ ሀገራት የተቀጣጠለው የተራማጅ ወጣቶች ንቅናቄ አዲስ የትግል ምዕራፍ እና አስተሳሰብን አመላካች ነበር፡፡ “ወንድማማችነት” ያስተሳሰረው የአንድ ሀገር ሕዝብ ኅብረት ፈጣን እና ምትሃታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ አብዝቶ ተሰበከ፡፡ በየጊዜው የተስተዋሉ እና የተከሰቱ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ስብራቶች ለፈጠሯቸው የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክቶች መቋጫ ያበጁ ሀገራት አዲስ ምዕራፍን አንድ ብለው ተራማጅ አስተሳሰቦችን መላበስ ጀመሩ፡፡

 

በሃሳብ ልዩነት ምክንያት የሚፈጠሩ ደም አፋሳሽ ግጭቶችን በማያዳግም መንገድ ቋጭቶ የሃሳብ ልዕልናን ለማስፈን የመጨረሻ ባሉት አብዮት ስኬታማ ለውጦችን ያመጡ ሀገራት ለቀሪው ዓለም ተራማጅ ወጣቶች ሞዴል እና አርዓያ ኾኑ፡፡

 

የአውሮፓ ሀገራትን እንደ ወረርሽኝ አዳርሶ ወደ ሩቅ ምሥራቅ ያቀናው የነጻነት አቢዮት መካከለኛው ምሥራቅን ተሻግሮም ወደ አፍሪካ አህጉር መቀጣጠሉ አልቀረም ነበር፡፡ ምንም እንኳን በአፍሪካ ሀገራት የተቀጣጠለው አቢዮት የታሰበለትን ያክል ለውጥ አለማምጣቱ ድክመት ተደርጎ ቢወሰድም፡፡

 

በዋናነት ማኅበራዊ ሱታፌ ፖለቲካዊ ርእዮተ ዓለምን እያነበነበ ከ1960ዎቹ መባቻ ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ የተስተዋለው ግራ ዘመም አቢዮት በመሳሪያ አንጋቾች ተጠምዝዞ ሃዲዱን ቢስትም ዝነኛው የፈረንሳይ አቢዮት ትሩፋቶች ኢትዮጵያ ውስጥም የትግል ጥያቄዎች ኾነው ሲቀነቀኑ ተደምጧል፡፡

 

ከ1960ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ የተቀሰቀሰው የተማሪዎች አቢዮት “መሬት ላራሹ” ብሎ ሲነሳ ስሜቱን ያልቆነጠጠው ተራማጅ ወጣት አልነበረም፡፡ ከወትሮው ለረጂም ዘመናት በዘውዳዊ ሥርዓት ማኅበር የቆረበችው ኢትዮጵያ የመጣችበት የሀገረ መንግሥት የምሥረታ መንገድ ብዙም እንደማያስቀጥላት ግን ለብዙኃኑ ተራማጆች እሙን ነበር ብለው የሚያምኑት በርካቶች ነበሩ፡፡

 

የውጭው ዓለም ተራማጅ የፖለቲካ ይትባህል የፈጠረው ቁጭት እና የተራማጅ ወጣቶቹ ቀናዒ ስሜት ብቻ ተዳምረው ለዘመናት በሀገሪቱ ስር በሰደደው ዘውዳዊ ስሪት ተጠልፎ ይወድቃል ተብሎ ቢጠበቅም የታሰበው ቀርቶ ያልታሰበው ኾኖ “እጁን በእጁ ቆረጠ” ተባለለት፡፡ አቢዮቱ በብሔር ተኮር የፖለቲካ ልሂቃን ጡዞ በወታደር አፈሙዝ እስኪበላ እና ተስፋ የሰነቁ ወጣቶች ከነራዕያቸው እስኪከስሙ ድረስ ኢትዮጵያ ዘመናትን ካስቆጠረው ዘውዳዊ ሥርዓት ነጻ ወጥታ ለማየት የጓጉት ልጆቿ እልፍ ነበሩ፡፡

 

የርእዮተ ዓለም እስረኝነት ኢትዮጵያ ውስጥ ለበለጠ ቅራኔ እንጂ ለበለጠ መፍትሔ እና ወንድማማችነት መንገድ ሲኾን አልተስተዋለም፡፡ ከታላቁ አብዮት መጠናቀቅ ማግስት ጀምሮ በመላው ዓለም ነጻነት፣ እኩልነት እና ወንድማማችነት የትግል ጥያቄዎች መሪ መፈክር ኾነው ተስተጋቡ፡፡ በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ግን በብዙዎች ዘንድ የተናፈቀው ወንድማማችነት ከሰባት አስርት ዓመታት በኋላ እንኳን እውን መኾን ተስኖት በተደጋጋሚ ጦርነት እና ግጭት ውስጥ ማለፍ ግድ እንዳለ ዘለቀ፡፡

 

በበርካታ ሀገራት ሕዝብን ከሕዝብ ነጣጥለው በመፈረጅ ደረጃ የሰጡ ነባር ማኅበራዊ ሥሪቶች በየቦታው ተናዱ፡፡ የሰው ልጅ በሕግ ፊት እኩል ነው፤ የዘር፣ የሃይማኖት እና የቆዳ ቀለም ልዩነት ሰውን በደረጃ ለይቶ ለመፈረጅ ብቁ አመክንዮዎች አይደሉም ተባለ፡፡ ምንም እንኳን ነባሩን አስተሳሰብ እና ፍረጃ ለማስወገድ ቀላል ባይኾንም ትግሉ አዲስ እይታ እና እሳቤን አሰፈነ፡፡ በወቅቱ የሚቀነቀኑ የነጻነት ጥያቄዎች በበርካታ ሀገራት ፈር እና መልክ የያዙ ስለነበሩ ሃሳብ ያሰባሰባቸው ተራማጅ ወጣቶችን በአንድ ለማሰባሰብ እና ለውጥ ለማምጣት ብዙም አስቸጋሪ አልኾኑም ነበር፡፡

 

ምንም እንኳን በበርካታ የዓለም ሀገራት ዘንድ ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ግጭቶች በከፍተኛ መጠን ቢቀንሱም እውነተኛ ወንድማማችነት ግን በብዙዎች ዘንድ ተዘነጋ፡፡  በርካታ ጸሐፍትም ደጋግመው እንደሚሉት ከፈረንሳይ አብዮት ትሩፋቶች መካከል አንዱ የኾነው ወንድማማችነት በበርካታ አካባቢዎች የትግል ንቅናቄ ውስጥ ተዘንግቷል ሲሉ ቅሬታቸውን ያስተጋባሉ፡፡ በሀገራት መካከል በእርስ በእርስም ኾነ በውጭ የሚስተዋሉ ቅራኔ የወለዳቸውን ግጭቶች ለማከም ወንድማማችነት ፍቱን መድሐኒት ነውም ይላሉ፡፡

 

እንደ አውሮፓዊያን የዘመን ስሌት በቅርቡ የካቲት 2019 አቡ ዲያቢ ላይ “የሰው ልጆች ወንድማማችነት ለዓለም ሰላም እና አብሮነት” በሚል ርእስ በሊቀ ጳጳሳት ፍራንሲስ እና በአል-አዝሃር አሃመድ አል-ታይብ ታላቁ ኢማም በተፈረመው የዓለም ሰላም ሰነድ ላይም “ያለወዳጅነት ሙሉ ሕይዎት ይኖራል ብለን አናምንም” ይላል፡፡ ነገር ግን ዛሬም ድረስ ወንድማማችነት በብዙ ሀገራት የነጻነት እና የእኩልነት መብት ትግሎች ውስጥ በመዘንጋቱ ላልተፈለገ የእርስ በእርስ ግጭት ሲዳርግ ይስተዋላል ሲሉም ይሞግታሉ፡፡

 

ታሪክ ያዛመዳቸው፣ ወንዝ ያስተሳሰራቸው፣ ማንነት እና ምንነት የገመዳቸው እና እጣ ፋንታቸው በአንድ የተቆራኘ ሕዝቦች የልዩነት ሰበዝ እየመዘዙ የብሔር እና የልዩነት ፖለቲካ መቃረናቸው ከፈረንሳይ አብዮት ትሩፋቶች መካከል አንዱ የኾነው “ወንድማማችነት” ተገቢው ቦታ ስለተነፈገው የመጣ ነው ብለው ያስባሉ፡፡ ፕሮፌሰር አንቶኒዮ ባጊዮ ወንድማማችነት የጥልን ግድግዳ አፍርሶ የፍቅር ድልድይን መገንባት የሚያስችል ኀይል አለው ይሉናል፡፡ ወንድማማችነት ተመሳሳይ ዓላማ እና መዳረሻ ያላቸውን ወጣቶች አሰባስቦ ለዓለም ሰላም የሚያደርስ ምትሃታዊ አብሮነት አለው፡፡

ኢትዮጵያ ለዘመናት በጸናው ታሪኳ ውስጥ ወንድማማችነት የተለየ ቦታ አለው፡፡ የሃይማኖት፣ ባሕል እና ማንነት ልዩነቶች ሳንካ ሳይኾኑባቸው ለአንድ ዓላማ በወንድማማችነት ቆመው ታሪክ አጽንተዋል፤ ሀገር ጠብቀዋል፡፡ ከዓድዋ እስከ ካራማራ በአንድ መቃብር አብረው የወደቁ፤ በአንድ ምሽግ ውስጥ የደቀቁ ወንድማማቾች ሕያው ምስክሮች ናቸው፡፡

 

በሃሳብ ልዩነት ምክንያት ቅራኔ ውስጥ የሚገቡ እና እርስ በእርሳቸው የሚፈላለጉ ወገኖች የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ምልክት ሳይኾን ሉዓላዊነት የፈጠረው የሴራ ፖለቲካ ምሳሌ ናቸው፡፡ የዘርፉ ምሁራን እና የዓለም ሰላም አሳቢዎች “ወንድማማችነት ከፖለቲካ ርእዮትም፤ ከሃሳብ ልዩነትም በላይ ነው” ይሉናል፡፡

 

ወንድማማችነት ሰይፍን ወደ ሰገባው መልሶ በፍቅር የሚያስተቃቅፍ ሃዲድ ነው፡፡ ፍጹማዊ ወንድማማችነትን ለመመስረት የሥሜት ብስለትን ይጠይቃል፡፡ ሌሎችን መቀበል፣ ራስን መቆጣጠር፣ ሰዎችን መረዳት እና መልካም ግንኙነትን መመስረት የስሜት ብስለትን ከፍ ያደርጋሉ፡፡ የስሜት ብስለቱ የላቀ ማኅበረሰብ እና ትውልድ የሃሳብ ልዩነት የግጭት መንስኤ ሳይኾን የችግር መሻገሪያ ድልድይ ኾኖ ያገለግላል፡፡ የሃሳብ ልዩነት ደግሞ መንገድን እንጂ መዳረሻን አይወስንም፡፡

 

ኢትዮጵያዊያን ስለኢትዮጵያ ያላቸው እይታ መንገዳቸውን እንጂ መዳረሻቸውን አይወስነውም፡፡ የእርስ በእርስ ጦርነት እና ግጭት ሰብዓዊ ኪሳራ፣ ምጣኔ ሃብታዊ ድቀት እና ውድመት ያስከትላል፡፡ በተለይም የእርስ በእርስ ጦርነትን አስከፊነት ለማሳየት ከኢትዮጵያ የተሻለ ምሳሌ ማፈላለግ አያስፈልግም፡፡

 

ጦርነት እና ግጭት የሚካሄድባቸው አካባቢዎች ከጦርነት ማግስት እንኳን ከተፈጠረው አስቀያሚ ድባብ በቀላሉ መውጣት ይሳናቸዋል፡፡ ኀያላኑ ሀገራት አይቀሬ ጦርነት በሜዳቸው ከመምጣቱ በፊት ከሜዳቸው ውጭ ሄደው የሚገጥሙት የጦርነትን ዳፋ ቀድመው ስለሚረዱት ነው፡፡ ግጭቱ እና ጦርነቱ የእርስ በእርስ ሲኾን ደግሞ አስከፊነቱን ለመረዳት ብዙ ርቆ መሄድን ሳይጠይቅ ጎረቤትን መመልከት ከበቂ በላይ ነው፡፡

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም እና የጋራ ትርክት
Next article“የወንጀል መከላከልና የምርመራ ሥራዎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እየተከናወኑ ነው” ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ