
ሰቆጣ: ሕዳር 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በድሃና ወረዳ ከመስከረም 20/2016 ዓ.ም ጀምሮ የኮሌራ ወረርሽኝ ተከስቶ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል። በወቅቱ በድሃና ወረዳ ሁለት ቀበሌዎች ላይ የተከሰተውን በሽታ ለመቆጣጠር ሰፊ ሥራ ሲሠራም ቆይቷል።
በተሠራው የርብርብ ሥራም በሽታውን መቆጣጠር እንደተቻለ በአምደወርቅ ጤና ጣቢያ የኅብረተሰብ ጤና አገልግሎት መከላከል እና መቆጣጠር ኦፊሰር ሲሳይ አያሌው ገልጸዋል። እንደ ባለሙያው ገለጻ የኮሌራ በሽታ በፈጣን ሁኔታ የሚዛመት እና ወረርሽኙ በገጠራማ አካባቢዎች የተከሰተ በመኾኑ የቁጥጥር ሥራውን አዳጋች አድርጎት ነበር።
የድሃና ወረዳ ጤና አጠባበቅ ጽሕፈት ቤት የፈውስ ሕክምና ኦፊሰር ወርቅነህ ታፈራ በሽታው በተከሰተባቸው አካባቢ ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙ በማድረግ እና የለይቶ ሕክምና በማድረግ ወረርሽኙን ሙሉ በሙሉ ከወረዳው ማጥፋት ተችሏል።
የድሃና ወረዳ ጤና አጠባበቅ ተወካይ ኀላፊ አሰፋ ዋሴ በወረዳው በሽታው እንደተከሰተ የጤና ባለሙያዎች በወሰዱት የኤክስቴንሽን ሥራ መቶ በመቶ በሽታውን መከላከል ተችሏል ነው ያሉት። በቀጣይም ወረርሽኙ እንዳይከሰት የለይቶ ሕክምና ክፍል በሦስት ጤና ጣቢያዎች በድንኳን እየተዘጋጀ ነው ብለዋል።
ክልሉ የላከውን የፍሉድ መድኃኒት በማዘጋጀት የኅብረተሰቡን ጤንነት በዘላቂነት ለመጠበቅ ዝግጁ እንደኾኑም አስገንዝበዋል። የኮሌራ በሽታን ለመከላከል ያልበሰሉ ፍራፍሬዎችን አለመመገብ፣ የግል ንጽሕናን መጠበቅ እና የቤት ቁሳቁሶችን በአግባቡ በንጽሕና መጠበቅ እንደሚገባ ምክረ ሃሳባቸውን አጋርተዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!