በደሴ ከተማ የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የመንግሥት ተቋማት የማበረታቻ እውቅና እና ሽልማት ተሰጠ።

46

ደሴ፡ ኅዳር 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ አሥተዳደር ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ “ማገልገል ክብር ነው፤ በቅንነት ማገልገል ደግሞ ድርብ ክብር ነው” በሚል መሪ መልእክት በከተማ አሥተዳደሩ የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ተቋማት የማበረታቻ እውቅና እና ሽልማት ሰጥቷል።

ሽልማቱ የተበረከተላቸው ተቋማቱ በ2015 ዓ.ም በወጣው የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም መሠረት ከሐምሌ 1/2015 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 12/2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ተገምግመው በአፈፃፀም እና በሥነ ምግባር ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ የወጡ ናቸው።

አሚኮ ያነጋገራቸው እውቅና የተሰጣቸው ተቋማት ተወካይ አቶ ሀሰን አበጋዝ እና ወይዘሮ ሙሉ አባቡ በሽልማቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል። ውጤቱ የመጣው በመላ ተቋማቱ ሠራተኞች ጥረት መኾኑንም ተናግረዋል።

በተቋማት መካከል የውድድር መንፈስ መፈጠሩ እና እውቅና መሠጠቱ ባለሙያዎች የተሻለ ሥራ እንዲሠሩ ለማነሳሳት እና የመልካም አሥተዳደር ችግር እንዲቀረፍ ያስችላል ያሉት ደግሞ የደሴ ከተማ አሥተዳደር ሲቪል ሰርቪስ መምሪያ ኀላፊ ሰለሞን በዛብህ ናቸው። ኀላፊው በቀበሌዎች ውስጥ ያሉ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ከክፍለ ከተሞች ጋር በጋራ እየሠሩ እንደኾነ አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ፦ አንተነህ ፀጋዬ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኅብረተሰቡን ጤና በዘላቂነት ለማሻሻል ቅንጅታዊ አሠራርን መዘርጋት እንደሚገባ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) አሳሰቡ።
Next articleተከስቶ የነበረውን የኮሌራ ወረርሽኝ ሙሉ በሙሉ መከላከሉን የድሃና ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ገለጸ።