
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ሁለተኛውን ዓለም አቀፍ የጤና ምርምር ጉባዔን አካሂዷል።
ጉባዔው የምርምርን ግንዛቤ ለማሳደግ፣ ወጣት ተመራማሪዎችን ለማበረታታት እና ከፍተኛ ተመራማሪዎችም ያላቸውን ልምድ ለወጣቶች እንዲያካፍሉ ዓላማ ያደረገ ነው።
ብቁ እና ጤናው የተጠበቀ አምራች ማኅበረሰብ ለመገንባት የጤናውን ዘርፍ ማዘመን ላይ ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) አሳስበዋል። ለዚህ ደግሞ መንግሥት ዘርፉን ለማሻሻል ከሚያደርገው ሥራ ባሻገር አጋር አካላት ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ነው የገለጹት።
በተለይም ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር፣ ለጤና ዘርፍ ችግር ፈች እና ብቁ የሰው ኀይል ማፍራት ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሠሩ አሳስበዋል። ማኅበረሰቡም የጤና ተቋማትን መጠበቅ እና መደገፍ እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት።
የአማራ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ የኅብረተሰቡን ጤና ዘላቂነት ባለው መንገድ ለማሻሻል ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በተለይም ደግሞ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምር ሥራዎችን ትኩረት አድርጎ እየሠራ መኾኑን አንስተዋል።
ሌሎች በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችም የጤናውን ዘርፍ በዕውቀት እንዲያግዙ ሥምምነት ላይ መደረሱን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የምርምር እና ስርፀት ዳይሬክተር ሙሉሰው አንዱዓለም (ዶ.ር) እንዳሉት ኮሌጁ በትምህርት፣ በምርምር፣ መረጃ በመሰብሰብ እና በሌሎችም ተግባራት ላይ ከጤና ቢሮ ጋር በጋራ እየሠራ ይገኛል።
ኮሌጁ ከሀገሪቱ ባሻገር በአፍሪካም ጭምር ደረጃውን የጠበቀ “ጣና የምርምር እና ዲያግኖስቲክ ማዕከል”ተቋም በመገንባት ለሥራ ዝግጁ ማድረጉን ገልጸዋል። የምርምር ተቋሙ ከምርምር ባለፈ ወደ ውጭ የሚላኩ ናሙናዎችን ለማስቀረት ያግዛል ብለዋል። ኮሌጁ በቀጣይ ችግር ፈች ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራም ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!