በዘንድሮው የመኸር ወቅት ከ200 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መሠብሠቡን የድሃና ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

33

ባሕር ዳር: ሕዳር 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በ2015/16 የምርት ዘመን ቆላማ አካባቢዎች ምርትን ቀድመው የሠበሰቡ ሲኾን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ደጋማ እና ወይናደጋ አካባቢዎች የሰብል መሠብሰቡ ሥራ እንደቀጠለ ነው።

ድሃና ወረዳ በዋግ ኽምራ ካሉ ደጋማ ወረዳዎች አንዷ ስትኾን የጥራጥሬ ሰብሎች ተሠብሥበው ተጠናቅቀዋል። የጤፍ እና የስንዴ ኩታገጠም ሰብሎች ግን ገና በመሠብሠብ ላይ መኾናቸውን የድሃና ወረዳ 01 ቀበሌ አርሶ አደሮች ተናግረዋል።

አርሶ አደር ታደለ አጥናፉ እንደገለጹት ከአሁን በፊት የባቄላ እና ማሽላ ምርት አስገብተዋል። ከጤፍ የተሻለ ምርት እንደሚያገኙም ተናግረዋል። ዲያቆን ፍቅረማርያም ታደሰ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በጤፍ ኩታገጠም ሰብላቸው ላይ በመጣሉ ምክንያት የጤፍ ምርታቸው ቢቀንስም በስንዴ ኩታገጠም ካለሙት ማሳ እስከ 30 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

የድሃና ወረዳ የሰብል ባለሙያ ወይዘሮ ፎትየን አረጋዊ እንደገለጹት የሰብል አሠባሠቡ ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንዳያበላሸው ለአርሶ አደሩ ትምህርት እና ግንዛቤ በመፍጠር በወበራ እና በኅብረት እንዲሠበሠብ አድርገናል ብለዋል።

የድሃና ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዘነበ ማሞ በወረዳው 28 ሺህ 693 ነጥብ 6 ሄክታር መሬት በሰብል መሸፈኑን ተናግረዋል። ከተሸፈነው 468 ሺህ 514 ኩንታል ምርት ለማግኘት እቅድ ተይዞ ሲሠራ መቆየቱንም ገልጸዋል።

ከ200 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መሠብሠብም ተችሏል ነው ያሉት። አቶ ዘነበ እንደገለጹት የምርት አሠባሠቡ ሥራ በተጠናከረ መንገድ ቀጥሏል።

ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እና የሰብል ተባይ ምርቱ ከተያዘው እቅድ 40 በመቶ እንዲቀንስ ማድረጉንም አስገንዝበዋል። በቀጣይ በመኸር ወቅት የቀነሰውን ምርት በበጋ መስኖ ለማካካስ ከወዲሁ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑንም አብራርተዋል። አርሶ አደሩ በፍጥነት ሰብሉን በመውቃት ማሳውን ለመስኖ እንዲያዘጋጅም ምክረሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም እና የጋራ ትርክት
Next articleየኅብረተሰቡን ጤና በዘላቂነት ለማሻሻል ቅንጅታዊ አሠራርን መዘርጋት እንደሚገባ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) አሳሰቡ።