የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም እና የጋራ ትርክት

28

ባሕር ዳር: ኅዳር 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ከሠላሳ ዓመታት በላይ እየተተገበረ ነው። ከቀድሞው የኢትዮጵያ የመንግሥት ሥርዓት ብቻ ሳይኾን ከሌሎች ሀገራት የፌዴራል ሥርዓትም እንደሚለይም የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ።

ከፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ተጠቀምን የሚሉ እንዳሉ ኹሉ ቅሬታ እና ጥያቄ የሚያነሱም አሉ። ከፌዴራሊዝም ሥርዓቱ በፊትም ኾነ በኋላ ‘አበርክቻለሁ’ የሚሉ እንዳሉ ሁሉ በሌላ በኩል ‘ተበድያለሁ’ የሚሉ ኃይሎች በሕዝብ እና በብሔር ሥም ዳር እና ዳር ወጥረውታል። በዚህ ቡራቡሬ አተያይ እና አቋም መሃል ኾኖ መንግሥት የከረረውን ለማርገብ፤ የራቀውን ለማቅረብ እና ችግሩን ለመቅረፍ ሲወጣ ሲወርድ ይታያል።

ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በጋራ የሚኖሩባት ኢትዮጵያን ከፍ ለማድረግና ሕዝቦችን የበለጠ ለማቀራረብ እና ለማግባባት እንዲያስችል ታምኖባቸው ከሚሠሩ ሥራዎች ውስጥ አንዱ ኅዳር 29 የብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ቀን አንዱ ነው።
በሌላ በኩል መንግሥት ከሚያለያዩ ነጠላ ትርክቶች አንድ ወደሚያደርጉ የጋራ ትርክቶች ያተኮሩ ተከታታይ ሥልጠናዎችን ለአመራሮች እየሠጠ ነው።

በእነዚህ እና መሰል ጉዳዮች ላይ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አህመድ ኑሩ እና በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት ክፍል የፌዴራሊዝም መምህር ሰይድ አሊ ሃሳባቸውን አካፍለውናል።

👉የፌዴራሊዝም ሥርዓት ለኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ምን ፋይዳ አለው?

በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አህመድ ኑሩ መሐመድ ”የፌዴራሊዝም ሥርዓት ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቋንቋ፣ ባሕል እና ማንነት ባሉባት ሀገር ሕዝቦች ማንነታቸው ታውቆ እና ተከብሮ በእኩልነት እንዲለሙ እና እንዲያድጉ በር ይከፍታል” ነው ያሉት።

አፈ ጉባኤው የአርጎባ ብሔረሰብ ”አሁን ላይ በፌዴራል ሥርዓቱ ማንነቱ ታውቆ፣ ራሱን እያሥተዳደረ እና እያለማ መኾኑን” ነው የገለጹት።

እየጠፋ የነበረ ቋንቋ፣ ባሕል እና ታሪኩን ማዳበሩን እና የመሠረተ ልማቶች ተጠቃሚነቱን ጠቅሰዋል አፈ ጉናኤው። ”በወረዳው የትምህርት ቤቶች ቁጥር ከ7 ወደ 31 ማደጋቸውን እና ሕጻናትም በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማራቸውን” በማሳያነት አክለዋል።

የአርጎባ ማኅበረሰብ በብዙ ኪሎ ሜትር ርቀት ያገኛቸው የነበሩትን የማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብት አገልግሎቶች በቅርብ ማግኘት መጀመሩም ሌላኛው የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ የጠቃሚነቱ ማሳያ መኾኑን አፈ ጉባኤ አህመድ አብራርተዋል።

በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት ክፍል የፌዴራሊዝም መምህር ሰይድ አሊ ፌዴራሊዝም ሥርዓት እንደየሀገራቱ ሁኔታ ሊለያይ እንደሚችል ገልጸዋል። ”የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ቋንቋ እና ብሔርን መሠረት ያደረገ ነው” ያሉት መምህሩ በሥርዓቱ ጥሩም መጥፎም ውጤት እንደታየ ገልጸዋል። ”ጥሩ የሚባለው የብሔር ብሔረሰቦችን ጥያቄ መመለሱ፣ በዚህም የብሔሮች ባሕል እና ቋንቋዎች ዕውቅና መሥጠቱ” መኾኑን ተናግረዋል። ብሔረሰቦች የመንግሥት ቅርጽ ይዘው ራሳቸውን በማሥተዳደር በሀገራዊ ፖለቲካው እንዲያንጸባርቁ ዕድል ፈጥሯልም ሲሉ አክለዋል።

👉የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም እና ሳንካዎቹ

”በሀገራችን ለዘመናት የነበረው የተዛባ ትርክት እንደማያዋጣ በሂደት ታይቷል” ያሉት አፈ ጉባኤ አህመድ ሀገራችን ለመበታተን አደጋ የሚያጋልጣት የእኔ አውቅልሃለሁ አስተሳሰብ እና የተሳሳተው የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት ናቸው ብለዋል።

መምህር ሰይድ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ሥርዓት አንዱ ድክመት ብሔርን ብቻ መሰረት በማድረግ መዋቀሩ መኾኑን ጠቅሰዋል። ‘ፓርቲዎች’ እና ‘ታጋዮች’ በጦርነት ሥልጣን እንደያዙ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን ችግር የብሔር ጥያቄ ብቻ ማስመሰላቸውን የውስንነቱ ምክንያት እንደኾነ ጠቅሰዋል። የራሳቸውን የፖለቲካ ፍላጎት ብቻ የሀገረ መንግሥቱ ሥርዓት ማድረጋቸው አሁን ላይ ለሚከሰቱት ችግሮች ሌላኛው ምንጭ እንደኾነም መምህሩ አመላክተዋል።

በብሔር ፖለቲካ የተቃኘው ሕገ መንግሥትም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያልተወያየበት፤ ከተሳሳተ ትርክት እና ከፓርቲ ሰነድ የመነጨ መኾኑን ያመላከቱት መምህር ሰይድ ”የተሳሳተው ትርክት እና የፓርቲ ሰነድም አንድን ብሔር ገዢ /ጨቋኝ/ መደብ በሚል ይፈርጃሉ” ብለዋል። የሕገ መንግሥቱ አርቃቂ ቃለ ጉባኤዎችም ይህንኑ እንደሚያመላክቱ ነው ምሁሩ ያብራሩት።

👉ኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት

መሪዎች በመሪነት ዘመናቸው ጥንካሬ እና ድክመት ቢኖራቸውም ዛሬ ላይ ሁሉንም ብሔሮች በእኩልነት ካካተተ ሥርዓተ መንግሥት ውጪ አማራጭ እንደሌለ አፈ ጉባኤ አህመድ ይናገራሉ።

እናም ይላሉ አፈ ጉባኤው ”እናም የተናጠል ትርክትን በማጉላት ከመጓተት ይልቅ የጋራ በኾኑት የባሕል፣ የሥራ እና የጀግንነት ታሪኮቻችን ላይ በማተኮር ከቁርሾ እና ከቂም ወጥተን መደመርን እና ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትን ማጎልበት ይገባል” ሲሉ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል። ከሚያናቁረን ይልቅ በሚያቀራርበን ታሪክ ላይ ተነጋግረን የወል ትርክትን ማጎልበት ይገባናል ሲሉም አክለዋል።

”ነጠላ ትርክትን ትተን የጋራ ትርክቶቻችን ማጉላት ማንም ጤነኛ ሰው የሚደግፈው ነው” ያሉት መምህር ሰይድ በበኩላቸው ”እውነተኛ ብሔራዊ ስሜት የሚፈጥር፤ ሀገሪቱ የሁሉም እና በሁሉም የተሠራች እንደኾነች የሚያሳይ ትርክትን ለማጉላት መንግሥት ቁርጠኛ ከኾነ የችግሮቻችን መውጫ በር ይኾናል” ሲሉም የጋራ ትርክት ማጉላትን ጠቀሜታ አስምረውበታል። ይሁን እና መንግሥት የራሱን ድርሻ ቢሠራም ፓርቲዎች እና ሕዝቦችም ሊወያዩበት እና አምነውበት ሊተገብሩት ይገባል ብለዋል።

👉ዜጎች፣ ብሔሮች፣ ፓርቲዎች እና መንግሥት እጃቸው ከምን?

በሕዝቦች መከባበር እና እኩል ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተች ኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የግጭት ምክንያት የኾኑትን ቁርሾዎች መተው አለብን ነው ያሉት አፈ ጉባኤ አህመድ። በውይይት እና በሃሳብ የበላይነት በማመን ነው ችግሮችን መፍታት አለብን ያሉት። አፈ ጉባኤው ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽኑን እንደ አንድ መፍትሔ መጠቀም እንደሚቻል አመላክተዋል።

የሚያልፉ ፓርቲዎች እና መንግሥት የማታልፈዋን ኢትዮጵያ ሲሉ ተነጋግሮ በመግባባት እና በሃሳብ የበላይነት በማመን እንዲሠሩ አሳስበዋል። ነጻ እና ገለልተኛ ተቋማትን የማጠናከሩን ሥራም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የተጋረጡባትን ችግሮች አልፋ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ተከባብረው በጋራ የሚኖሩባት ሀገር እንድትኾን ”ትልቁ ድርሻ በርካታ አቅሞች ያሉት የመንግሥት ነው” ያሉት የፌዴራሊዝም መምህሩ መጀመሪያ መንግሥት መዋቅሩን ማጥራት ይጠበቅበታል ብለዋል።

የመንግሥት ባለሥልጣናት በሚናገሩት ንግግር የሚያስተላልፉት የሕዝብ ቁጣ እና ጥርጣሬን ሊፈጥር ይችላል እና መጠናትም መታረምም አለበት ነው ያሉት። ፖለቲከኞች መረጃም ማስረጃም የማያቀርቡበትን ነገር እንደፈለጉ እንዲናገሩበት መፍቀድ እንደማይገባ እና እርምጃ የመውሰድን አስፈላጊነት ጠቁመዋል።

”እስካሁን የነበረውን የኢትዮጵያን የሺህ ዘመናት ችግር ለአንድ ማኅበረሰብ የማሸከም ትርክት ትልቁ የፖለቲካ ብልሽታችን ስለኾነ በማረም እንዲስተካከል ማድረግ” ሌላኛው መፍትሔ እንደኾነ የፌዴራሊዝም ምሁሩ ጠቅሰዋል።

ለብሔራዊ መግባባት የብሔራዊ እርቅ ኮሚሽኑ ገንቢ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የጠቀሱት መምህሩ የፖለቲካ ፍላጎቶች በእኩልነት ተስተናግደው እና ውይይት ተደርጎባቸው አሸናፊው ሃሳብ ሊለይ ይገባል ብለዋል። ሽግግሩን የሚመራም ነጻ እና ገለልተኛ አካል መሰየም እንደሚያስፈልገው ነው የገለጹት። መንግሥት የመሰረተው ፓርቲም እንደ አንድ ባለድርሻ አካል ብቻ መሳተፍ እንዳለበት ሃሳባቸውን አክለዋል።

”ለውጥ በሂደት እንጂ በአንድ ጊዜ አይመጣም” ያሉት መምህር ሰይድ መንግሥት የሚጠበቅበትን ሲወጣ ሌሎቹ አካላትም በመተባበር ሊሠሩ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በዓለም ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት እጅን ባለመታጠብ ምክንያት በሚመጡ በሽታዎች ይሞታሉ” የአማራ ክልል ጤና ምክትል ቢሮ ኃላፊ ገሰጥ ጥላሁን
Next articleበዘንድሮው የመኸር ወቅት ከ200 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መሠብሠቡን የድሃና ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።