“በዓለም ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት እጅን ባለመታጠብ ምክንያት በሚመጡ በሽታዎች ይሞታሉ” የአማራ ክልል ጤና ምክትል ቢሮ ኃላፊ ገሰጥ ጥላሁን

27

ባሕር ዳር: ኅዳር 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም ለ15ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ለ14ኛ ጊዜ የሚከበረው የዓለም የእጅ መታጠብ ቀን በክልል ደረጃ በባሕር ዳር የማስጀመሪያ ሥነ ስርዓት ተካሂዷል። በሥነ ስርዓቱ የልዩ ልዩ ተቋማት መሪዎች እና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የውኃ ሃይጅን እና ሳንቴሽን አስተባባሪ ሳሙኤል ከሀሊ በቀላሉ ልንተገብረው የሚገባ ነው ብለዋል። በቀላሉ መተግባር የሚቻለውን መተግበር ባለመቻል አሁንም ሕፃናት ይሞታሉ፣ ወገኖች ለተቅማጥ ይጋለጣሉ፣ በርካቶችም የመተንፈሻ አካላቸው ላይ ችግር ይፈጠርባቸዋል ነው ያሉት። የመታጠብን ባሕል በማሳደግ በሽታን መከላከል እንደሚገባም አመላክተዋል።

ከመመገብ በፊት፣ከተመገቡ በኋላ፣ ከመፀዳጃ መልስ፣ ሕፃናትን ከመንከባከባችን በፊት እና በኋላ መታጠብ በርካታ በሽታዎችን ለመከላከል ያስችላል ነው ያሉት። በዓሉን ትርጉም ሰጥቶ ማክበር ግንዛቤ እንዲፈጠር እንደሚያደርግም ገልፀዋል።

እጅን በአግባቡ መታጠብ የተቅማጥ በሽታን ከ23 እስከ 40 በመቶ ድረስ ይቀንሳል ነው የተባለው። ተማሪዎችን ከትምህርት ቤት እንዳይቀሩ ለማድረግ እና የጤና ተቋማትን ጫና ለመቀነስ እንደሚያግዝም ጠቁመዋል። ትራኮማን እና ሌሎች የቆዳ በሽታዎችን መከላከል ይቻላልም ብለዋል።

እጅ መታጠብ በሽታ አምጭ ጀርሞችን በቀላሉ መከላከል እና በሽታ የመተላለፉን እድልን ለማቋረጥ እንደሚረዳም አመላክተዋል። እጅ መታጠብ የኮሮና ቫይረስን ለመከለካል ትልቅ አስተዋፅዖ እንደነበረውም አስታውሰዋል። የኮሮና ቫይረስ የእጅ መታጠብ ባሕል እንዲያድግ እንዳደረገውም ገልፀዋል። እጅ መታጠብን በትምህርት ቤቶች እና በሌሎች ተቋማት መተግበር እንደሚገባም አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች ሕፃናት ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሴቶች ንቅናቄ ተሳትፎ ማስፋፊያ ዳይሬክተር ደስታ ፈንታ ሴቶች ንፅሕናቸውን ከጠበቁ ልጆች እና ማኅበረሰቡ ጤናማ የመኾን እድሉ ሰፊ ነውም ብለዋል። በከተማ ላይ እጅ መታጠብ እምብዛም ችግር ላይሆን ይችላል ያሉት ዳይሬክተሯ በገጠሩ ክፍል ችግሮች መኖራቸውን ገልፀዋል።

ሴቶች ንፅሕናቸውን እንዲጠብቁ እና በሽታን እንዲከላከሉ እንደቢሮ እየሠሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሀይጅን እና ሳንቴሽን ባለሙያ ገብሬ ቢራራ፤ በአማራ ክልል ባሉ ትምህርት ቤቶች ያለው የውኃ ሽፋን ዝቅተኛ መኾን እጅን በአግባቡ ለመታጠብ እንደማያስችል አንስተዋል። በትምህርት ቤቱ ያለውን ችግር መፍታት ካልተቻለ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለውን ችግር መፍታት አይቻልም ነው ያሉት። የውኃ አቅርቦት ከሌለ ተማሪዎች ለበሽታ እንደሚጋለጡ፣ ከትምህርት እንዲቀሩ እና ለሌላው ማኀበረሰብ እንዲያስተላልፉ እንደሚያደርግም ገልፀዋል።

ትምህርት ቤቶች መፀዳጃ፣ ውኃ እና የሴቶች ንፅሕና መጠበቂያ ቤት እንዲኖራቸው እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። ትምህርት ቤቶችን የተሟሉ ማድረግ ተማሪዎች ጤናማ ሆነው ትምህርታቸውን እንዲከታታሉ፣ የመቅረት ምጣኔ እንዲቀንስ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ትውልድ መፍጠር ያስችላል ነው ያሉት። ሃይጅ እና ሳንቴሽንም በትምህርት ቢሮ ደረጃ በትኩረት እየተሠራበት መኾኑንም አመላክተዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ገሰጥ ጥላሁን፤ እጅ መታጠብ ራስን ከበሽታ የሚከላከሉበት ቀላል እና ወሳኝ መንገድ ነው ብለዋል። በዓለም ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት እጅን ባለመታጠብ ምክንያት በሚመጡ በሽታዎች እንደሚሞቱም ገልፀዋል። የእጅ ባለመታጠብ በርካታ በሽታዎች እንደሚከሰቱም አመላክተዋል። እጅን በአግባቡ እና ሁልጊዜ መታጠብ የሕፃናትን ሕመም እና ሞት እንደሚቀንስ፣ ተላላፊ በሽታዎችን መከለከል እንደሚያስችልም ገልፀዋል።

ማኅበረሰቡ እጅን በአግባቡ እና ሁልጊዜ በመታጠብ ራሱን ከበሽታ መከላከል እንደሚጠበቅበትም አሳሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዓባይ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር 22 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር የአረቦን ገቢ አስመዘገበ፡፡
Next articleየኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም እና የጋራ ትርክት