ዓባይ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር 22 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር የአረቦን ገቢ አስመዘገበ፡፡

39

አዲስ አበባ: ኅዳር 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ዓባይ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር 22 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር የአረቦን ገቢ ማስመዝገቡን አስታውቋል፡፡ የዓባይ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር 13ኛ መደበኛ እና 12ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔውን አካሂዷል። ባለአክሲዮኖች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የዳሬክተሮች ቦርድ አባላት በተገኙበት እንደ አዎሮፓውያን አቆጣጠር የ2022/23 በጀት ዓመት የኩባንያውን አጠቃላይ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርቧል።

የአክሲዮኑ የቦርድ ሰብሳቢ አባተ ስጦታው በበጀት ዓመቱ ማጠናቀቂያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው 22 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር የአረቦን ገቢ ማስመዝገቡን ተናግረዋል። ከተመዘገበው 70 በመቶ የሚኾነው በግሉ ዘርፍ ያሉ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ድርሻ ነው ተብሏል።

ዓባይ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር ከጠቅላላ የአረቦን መጠን ውስጥ 681 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በማስመዝገብ 3 በመቶ የሚኾነውን የገበያ ድርሻ መያዝ መቻሉ እና ከባለፈው ዓመት ከተመዘገበው ገቢ ጋር ሲነጻጸርም የ61 በመቶ እድገት እንዳለው በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

አቶ አባተ ኩባንያው በሀገሪቱ የጸጥታ ችግር ምክንያት ተግዳሮቶች ቢያጋጥሙትም የኢንሹራንስ ገበያው አሁን ካለበት ደረጃ የበለጠ እንዲያድግ የሚያስችሉ አጋዥ ምክንያቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል። እየተሥፋፋ የመጣው የውጭ ኢንቨስትመንት፣ ስለመድኅን ዋስት የኅብረተሰቡ ግንዛቤ ማደግ እና መጨመር ኩባንያው ከፍ እንዲል አስተዋጽኦ ካደረጉት መካከል ናቸው።

አማራ ክልል ላይ ያለው የጸጥታ ችግር በኩባንያው ላይ ተጽዕኖ መፍጥሩን እና በትግራይ ያለው የመቀሌ ቅርንጫፍ ሥራ አለመጀመሩም በሪፖርቱ ተነስቷል።

ዘጋቢ:- ራሔል ደምሰው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“እንደ ሀገር መኖር ከተፈለገ ብዝኅ ማንነትን እንደ እድል ቆጥሮ በእኩልነት መኖር ያስፈልጋል” ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ
Next article“በዓለም ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት እጅን ባለመታጠብ ምክንያት በሚመጡ በሽታዎች ይሞታሉ” የአማራ ክልል ጤና ምክትል ቢሮ ኃላፊ ገሰጥ ጥላሁን