
ባሕር ዳር: ኅዳር 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 18ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል በጅግጅጋ ከተማ እየተከበረ ነው። በአከባበሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳሕለ ወርቅ ዘውዴ ኢትዮጵያ ባለ ብዙ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ሀገር እንደመኾኗ መጠን ብሔራዊ አንድነቷ የበለጠ እንዲጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል። የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓል የሚከበረው ብዙኅነት እና አንድነት የማይነጣጠሉ መኾናቸውን ለማሳየት ብቻ ሳይኾን ለማጠናከርም ነው ብለዋል።
ብዙኀነታችን በአንድነታችን እና በእኩልነታችን ላይ መሰናክል እንዳይኾን እንቅስቃሴዎቻችን ሁሉ አንድነታችንን በማይጎዱ መልኩ መፈጸም አለባቸው ሲሉም ፕሬዚዳንቷ አሳስበዋል። ማንነት ላይ የተመሰረቱ አደጋዎች በተለያዩ ሀገራት ላይ ይገጥማሉ፤ እንደ ሀገር መኖር ከተፈለገ ግን ብዝኅ ማንነትን እንደ እድል ቆጥሮ በእኩልነት መኖር ያስፈልጋል ሲሉ አብራርተዋል።
ባለፉት ዓመታት የተከበሩ የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓላት የበለጠ አቀራርበውናል፤ አስተዋውቀውናል፤ አብረን በልተናል፤ ተደስተናል ብለዋል። ይህንን የበለጠ ለማጠናከር እና የላቀ ሀገራዊ አንድነትን ለመገንባት ምን ሠራን? ብለን እያንዳንዳችን ራሳችንን መጠየቅ እንዳለብን ገልጸዋል።
ትኩረታችን የአንድ ቀን በዓል ላይ ብቻ እንዳይኾን መጠንቀቅ አለብን፤ በየቀኑ እና ከዓመት ዓመት ያለው አንድነታችን እና አብሮነታችን መገምገም አለበት ሲሉም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ በሕዝቦች መካከል የአንድነት ችግር የለም ሲሉም ፕሬዚዳንቷ አረጋግጠዋል። “የኢትዮጵያ ትልቅነት ከሕዝቦቿ ትልቅነት የሚመነጭ ነው፤ ኢትዮጵያ የሕዝቦች ታሪክ፣ ጀብዱ ባሕል እና ታታሪነት ድምር ውጤት ነችና” ሲሉም ገልጸዋል።
በዓለም ደረጃ የተደነቁ ብሎም ለዓለም የተበረከቱ ድንቅ ቅርሶችን ያበረከተች ሀገር አለችን፤ ሀገር በተጠቃች ጊዜ ሁሉ ሆ ብሎ በመነሳት ወራሪን መክተው ዳር ድንበር ያስከበሩልን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ልጆች ነን፤ ሀገራችንን ታላቅ ያደረጓት ሕዝቦቿ ናቸው ሲሉም ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ተናግረዋል።
እኛም የአሁኖቹ ኢትዮጵያዊያን ሀገርን ጠብቆ ማቆየት ብቻ ሳይኾን ኀላፊነት እና ግዴታ የሚሰማን ሀገር ወራሾች መኾናችንን መገንዘብ አለብን ብለዋል። የምንፈጽማቸው ድርጊቶች እና የምንናገራቸው ቃላት መጣጣም አለባቸው ነው ያሉት። ይህ ካልኾነ ግን ሀገር ወዳድነታችን በተግባር የሚለካ ውጤት ሊያመጣ እንደማይችል አስገንዝበዋል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ክፉኛ ተፈትናለች እየተፈተነችም ትገኛለች፤ ታሪኩ የውጭ ጠላትን መቅጣት ኾኖ ሳለ እርስ በራሳችን ጦር መማዘዝ ጀምረናል፣ ወንድም በወንድሙ ላይ ጭካኔ የተሞላበት ተግባር ከማድረግ መቆጠብ አለብን ሲሉም ተናግረዋል።
የንጹሀን ደም መፍሰስን፣ የትምሕርት መቋረጥን፣ የምግብ እጦትና ርሃብ በኢትዮጵያዊያን ላይ ሲፈራረቅ አይተናል፤እያየን ነው፤ ከሁሉም በላይ የሚያሳስበው ግን በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያዊነትን እያሳነስን እየሄድን መኾኑን አለመገንዘባችን ነው ብለዋል። ከሀገር ይልቅ ብሔርን እያስቀደምን፣ የሚያያይዘንን ማጣበቂያ ኢትዮጵያዊነት እንዳናጣ ልንሰጋ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
ለኢትዮጵያዊነታችን ከፍ ያለውን ቦታ መስጠት አለብን እንጂ በጠበብን ቁጥር የቆምንበትን ግንድ መገንጠል የለብንም፤ ስለዚህ አቅጣጫችንን እናስተካክል ሲሉም መክረዋል። ዘር እና ሃይማኖትን የፖለቲካ መጠቀሚያ መሳሪያ በማድረግ እስከ ድሃው ገበሬ የሚዘልቅ አዙሪት በሀገር ላይ አናድርግ ብለዋል።
ፕሬዚዳንቷ ኢትዮጵያ በሰላም የምትኖረው እና የምትለማውም የጋራ ችግራችንን ተነጋግረን ስንፈታ ብቻ ነው ሲሉም ገልጸዋል። ከአያገባኝም ስሜት ወጥተን ጥቃት እና ጥፋትን በጋራ መከላከል ይገባል ሲሉም ተናግረዋል። የሀሳብ ልዩነት ጠላትነት አለመኾኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንቷ የየራሳችንን አስተሳሰብ በማቅረብ እና በመወያየት ችግርን መፍታት እንጂ “ወደአፈሙዝ አማራጭ ማምራት ፈጽሞ ሊያከትም ይገባል” ብለዋል።
እኛ ኢትዮጵያውያን መነጋገርን፤ የሌላውን ሀሳብ መስማትን እና ተሟግቶ ማሸነፍን በቅጡ መለማመድ አለብን ሲሉም ተናግረዋል። ዘር፣ ሃይማኖት እና መሰል ጉዳዮችን ለሌላ ጠቀሜታ እያዋልን ሕዝባችን በገዛ ሀገሩ መንከራተት ይበቃዋል፤ የሀገሪቷ ሕግ ለሁሉም እኩል ተፈጻሚ መኾን አለበት፤ ማኅበራዊ መስተጋብራችንን አናናጋ፤ “የጋራ መርከባችንን አንነቅንቃት” ብለዋል። ግፍና ጥላቻን በጽኑ እንጸየፍ፤ ሞት ሲመጣ ይምጣ እንጂ አንለማመደው ሲሉም ፕሬዚዳንቷ አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!