”የአካል ጉዳተኞችን ችግር ለመቅረፍ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊያበረክት ይገባል” የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ

49

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አቶ አወቀ ተመስገን ባለበት የአካል ጉዳት ራሱን ችሎ መራመድ ይቸገራል። ከባሕር ዳር የአካል ተሐድሶ ማዕከል የመጓጓዣ ብስክሌት አግኝቷል። ”ያለ ተሽከርካሪ ስጓዝ ድካም ብቻ ሳይኾን ጊዜም ይወስድብኝ ነበር፤ የመጓጓዣ ተሽከርካሪ ድጋፍ በማግኘቴ ድካሜም፣ ጊዜም ይቀንሳል” ብሏል።

አቶ ቢላል ሽፈሬ ለሕጻን ልጃቸው የመራመድ ችግር የመንቀሳቀሻ ተሽከርካሪ (ዌል ቸር) ድጋፍ ተደርጎላቸዋል። ልጃቸውን የሚያንቀሳቅሱት በሸክም እንደነበር እና እያደገ ሲመጣም ተሸክሞ ለማንቀሳቀስ ይቸገሩ እንደነበር ተናግረዋል። ለልጃቸው የተደረገው ድጋፍም ችግራቸውን ስለሚቀንስላቸው አመሥግነዋል።

የባሕር ዳር አካል ተሐድሶ ማዕከል ሥራ አሥኪያጅ ያለምወርቅ ይታየው ማዕከሉ ለአካል ጉዳተኞች የተለያዩ የድጋፍ ቁሳቁሶችን እያመረተ እንደሚደግፍ ገልጸዋል። ከአመልድ ኢትዮጵያ በተደረገ የ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ የማዕከሉን ሥራ የሚያቃልሉ ግንባታዎች እና ቁሳቁሶች መሟላታቸውንም ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ንጹህ ሽፈራው፤ ቢሮው ከኅዳር አጋማሽ ጀምሮ ለአቅመ ደካማ አካል ጉዳተኞች የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ የአካል ጉዳተኞች ቀንን አክብረዋል።

የባሕር ዳር አካል ተሐድሶ ማዕከል በክልሉ መንግሥት ለማዕከሉ ከፍተኛ በጀት የሚመደብለት ቢኾንም ከእረጂ ድርጅቶች መካከል አመልድ ኢትዮጵያ ባደረገው ድጋፍ የተሠሩ ሥራዎችን ጎብኝተናል፤ ይህም አካል ጉዳተኞች የሚሠራውን ሥራ አውቀው እንዲገለገሉበት ለማስተዋወቅ ነው ብለዋል።

የአካል ተሐድሶ ማዕከሉን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የመሠረተ ልማት ግንባታዎች መስፋፋት እና የቁሳቁስ አቅርቦት ያስፈልገዋል ያሉት ምክትል ኀላፊዋ ”የአካል ጉዳተኞችን ችግር ለመቅረፍ ሁሉም ሰው የበኩሉን ድርሻ ሊያበረክት ይገባል” ብለዋል።

በአማራ ክልል በባሕር ዳር፣ በጎንደር እና በደሴ የአካል ጉዳተኞች ማዕከል መኖራቸው እና የባሕር ዳር አካል ተሐድሶ ማዕከል እስካሁን ድረስ በምዕራብ አማራ ለ1 ሺህ 500 የአካል ጉዳተኞች የመጓጓዣ ተሽከርካሪ (ዌል ቼር) ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል።

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሀገር እንደ ሀገር ጸንታ እንድትቀጥል ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት ብቻ በቂ ነው” አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር
Next articleተጠባቂው የሸገር ደርቢ ጨዋታ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዘመ።