“ሀገር እንደ ሀገር ጸንታ እንድትቀጥል ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት ብቻ በቂ ነው” አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

33

ባሕር ዳር: ኅዳር 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል በሶማሊ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች እየተከበረ ነው፡፡ በዓሉ የኢትዮጵያ ቀን ኾኖ “ብዝኃነት እና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት” በሚል መሪ መልእክት እየተከበረ ነው፡፡

በዓሉ ሀገራዊ አንድነትን ለማጽናት ፋይዳ ያለው ነው ያሉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ኢትዮጵያዊያን ከልዩነት ይልቅ አንድነትን፣ ከመራራቅ ይልቅ መቀራረብን እና ከመጠራጠር ይልቅ መተማመን ላይ እንዲደርሱ አግዟል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ የብዝኃነት ሀገር ናት ስንል ኅብረ ብሔራዊ ማንነት አላት ማለታችን ነው ያሉት አፈ ጉባኤው መርሗ እኩልነት ነው ብለዋል፡፡ የጠቅላይነት እና ነጣይነት አስተሳሰብን በመተው ብዝኃነትን በአግባቡ ማስተናገድ ከተቻለ ለሀገራዊ አንድነት ጉልበት መኾኑን አምኖ መቀበል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን በተለያየ የታሪክ አጋጣሚ በጋራ ወድቀው ያጸኗት ሀገር አለቻቸው ያሉት አፈ ጉባኤው አንድነትን እና ኅብረ ብሔራዊነትን አጽንተው ለመቀጠል የሚያስችል እርሾ አቆይተዋል ብለዋል፡፡ ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ የተፈጠሩ በርካታ ፈተናዎች ቢኖሩም ችግሮችን በጽናት እና በብስለት ለማለፍ የተደረገው ጥረት አበረታች ውጤት አምጥቷል ነው ያሉት፡፡

“ሀገር እንደ ሀገር ጸንታ እንድትቀጥል ሁላችንም የየድርሻችንን መወጣት ብቻ በቂ ነው” ብለዋል የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር።

ከአስር ዓመት በፊት የሶማሊ ክልል ለመጀመሪያ ጊዜ በዓሉን ሲያስተናግድ የፀጥታ ስጋቶች እንደነበሩበት አንስተው አሁን ላይ ለኅብረ ብሔራዊቷ ኢትዮጵያ ተምሳሌት መኾን የቻለ ክልል መኾኑን አንስተዋል፡፡

በታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያዊያን በዜግነት ድርና ማግ ኾነን የምንኖር ሕዝቦች ነን” ሙስጠፋ ሙሐመድ
Next article”የአካል ጉዳተኞችን ችግር ለመቅረፍ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊያበረክት ይገባል” የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ