“ቀምበር አሠቃይ፤ ዘር አሥነቃይ”

61

ባሕር ዳር: ኅዳር 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)አርሰው ነጭ እና ጥቁር የሚያመርቱት፣ ጎተራውን የሚያስጨንቁት፣ ገበያውን የሚያጠግቡት፣ ከራሳቸው አልፈው ሀገሬውን የሚመግቡት፣ ከጓሮው እሸት፣ ከግሬራው ወተት የማያጡት፣ ሆዳቸውን ከሚያስገምቱ ኩራት እራት ብለው ጦማቸውን የሚያድሩት፣ አልጋ ለቀው እንግዳ የሚያሳድሩት፣ ወጭና ወራጁን፣ አላፊ አግዳሚውን የሚያበሉት፣ የሚያጠጡት፣ ስንቅ አስይዘው፣ ፈረስ ጭነው የሚሸኙት እነዚያ ኩሩዎች ቀን ጣላቸው፤ ወቅት ገፋቸው፡፡

ቀምበር የሚያሰጥል፣ ዘር የሚያስነቅል የችግር ጊዜ ገጠማቸው፡፡ በሰፊው ማረስ፣ በሰፊው ማፈስ፣ በሰፊው ማጉረስ፣ አሳምሮ መልበስ እና ማልበስ የሚያውቁት እጅ አጠራቸው፤ እንኳን ለእንግዳ የሚያጎርሱት ለልጆቻቸው የሚሰጡት አነሳቸው፡፡ ክፉ ወቅት ኩሩዎችን ምግብ አስጠየቃቸው፣ ሆዳቸውን የማያስገመግሙትን የሰው እጅ አሳያቸው፡፡ ልጆቻቸውን ለሰው የማያሳዩት፣ ሲመገቡ የማያሳዩት፣ በጓዳ ሸሽገው የሚያጎርሱት ወቅት ገፍቷቸው ከሰው ፊት ቀረቡ፡፡

ጓጉተው የሚጠብቁት፣ ናፍቀው የሚዘጋጁለት፣ ሞፈርና ቀምበራቸውን አዘጋጅተው፣ ማረሻቸውን አሹለው፣ ዘራቸውን ቋጥረው፣ ወይፈን እና በሬዎቻቸውን አሳምረው የሚጠብቁት፣ አምላካቸውን አምነው የቋጠሯትን ዘር የሚበትኑበት፣ ጥቂት ዘር በትነው እልፍ የሚጠብቁት የክረምት ወቅት ቀረባቸው፡፡ ክረምት ከሌለ እራት የለምና ክረምቱ ሲቀር ሀዘን በረታባቸው፡፡ ችግር ከበባቸው፡፡

ለወትሮው ግንቦት ሲመጣ፣ ሰኔ ሲከተል ማለዳ ወጥተው በጨለማ የሚገቡት፣ ሲያርሱ ውለው የማይደክሙት እነዚያ ብርቱ ገበሬዎች አርሶ መዝራት፣ ዘርቶ ማረም፣ አርሞ ማጨድ ናፍቋቸው ከረመ፡፡ እንደወትሮው መስሏቸው የግንቦትን መምጣት፣ የሰኔን መተካት ተመልክተው በሬዎቻቸውን ጠምደው፣ ማሳቸውን አለስልሰው ዘር በትነው ነበር፡፡ ዳሩ ዝናብ በምድሯ አልወረደም፤ ምድርም እርጥበት አግኝታ አልረሰረሰችም እና ዘር ሳይበቅል ቀረ፡፡ “ዘር ቆርጥም ዘመን ማለት ይሄ ነው” ይሉታል እነዚያ ደጋጎች፡፡

በዘመናቸው ክረምት ሲቀር አይተው የማያውቁ ደጋጎች ክረምት ሲቀር ሲያዩ ሀዘናቸው የከፋ ኾነባቸው፡፡ ክረምቱን ሳያዩ አልፈዋል እና ሲርባቸው የሚጎርሱት አጥተዋል፡፡ በአማራ ክልል በስሜን ጎንደር ዞን በተከሰተ የዝናብ እጥረት ወገኖች ለችግር ተጋልጠዋል፡፡ እጃቸውንም ለእርዳታ ዘርግተዋል፡፡

በጃና አሞራ ባሕር አምባ በተሰኘች ሥፍራ የሚኖሩት ጥጋቡ ዋካው ስለ ድርቁ ሲነግሩን ዝናብ ትቶን ከረመ፤ እህል አልበቀለም፤ ሀገሩ ጥረጊያ ኾኖ ነው የታየው ነው ያሉን፡፡ ለችግር ተጋልጠናል፤ መንግሥትም ምላሽ ሊሰጠን ይገባል ይላሉ፡፡

በዘመናቸው እንዲህ አይነት ድርቅ አይተው እንደማያውቁ የሚናገሩት ጥጋቡ “እንኳን እኛ ከተወለድን በአባቶቻችን ዘመንም እንዲህ አይነት ድርቅ ታይቶ አይታወቅም፤ እኛም ከአባቶቻችን እንዲህ አይነት ድርቅ ሰምተን አናውቅም፡፡ በእርግጥ ድርቅ ይከሰት ነበር፤ ግን ያ ድርቅ ዘር የሚገኝበት፣ የእለት ጉርስ የማይታጣበት ድርቅ ነበር፤ የዘንድሮው ግን ምንም የበቀለ ነገር የለም፤ ከብቶቻችን አደጋ ላይ ወደቁ፤ በሬዎቻችንን ልንሸጥ ብንል ማን ይግዛን፣ በእርካሽ እንኳን ግዙን ብንል የሚገዛን አጣን ” ነው ያሉት፡፡

ደመና ያልተጎተተበት፣ ጎርፍ ያልተሰማበት፣ ወንዞች ያልደነፉበት፣ ተራራዎች በልምላሜ ያልተዋቡበት፣ እንስሳት ለምለም ሣር ያልቀጠፉበት አስከፊ የክረምት ወቅት፡፡ “አከራረማችን በተንጠልጠል ነው፤ በችግር ከረምን፤ የነብስ ማደሪያ እየተሰጠን ከረምን፤ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ ምን ይበላሉ፤ እስክብሪቶ እና ደብተርስ የት ያግኙ፣ አሳዛኝ ነገር ነው የገጠመን” ነው የሚሉት፡፡

ረሃብ የሚመርጠው ባይኖርም ሕጻናት እና አዛውንት ላይ ግን የከፋ እንደኾነም ነግረውናል፡፡ “ሕጻናት፣ ታላላቅ አባቶች እና እናቶች የከፋ ነገር አለ፤ በረሃቡ ምክንያት ሕመምም ተፈጠረ፡፡ እስካሁን አይተነው የማናውቀው ሙቀት ተፈጠረ፡፡ ወባም መጣ፡፡ በሽታ ኅብረተሰቡን አሰቃይቶታል” ብለውናል፡፡ ጋሽ ጥጋቡ ጉልበት ያለው ተሰድዶ ሥራ ወዳለበት አካባቢ ሄዶ እንዳይበላ እንኳን በክልሉ ያለው የሰላም ችግር አላንቀሳቅስ ብሏል ነው ያሉት፡፡

“ከእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ” እንዲሉ አበው ሠርተው ለመብላት ከቀያቸው ወጥተው የሄዱ ዘመዶቻቸው መንገድ ላይ ታግተው ገንዘብ ክፈሉ ተብለው፣ በሌለ ቤታቸው የሀገሬው ሰው አውጥቶ እንደከፈለም ነግረውናል፡፡ “ሌላ አካባቢ ሄደን እንዳንሠራ መንገዱ አላንቀሳቅስ አለ፡፡ የምናደርገው ግራ ገብቶን ነው ያለነው፣ የቀን ጨለማ ውጦን ነው ያለን” ነው ያሉት የችግሩት ስፋት እና ጥልቀት ሲነግሩን፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጥቂት ድጋፍ ቢኖርም ካለው ችግር እና ምንም የሌለን ከመኾናችን አንጻር በቂ አይደለም ብለውናል፡፡ “መንግሥትን እና የሚያዝኑ ወገኖችን የምንጠይቀው በመጀመሪያ የዕለት ቀለባችንን ነው፡፡ ፈጣሪ ፊቱን ቢመልሰው እና ዝናብ መጥቶ ዘር እንዝራ ቢባል የሚዘራ ዘር የለም፤ በምንስ አርሰን እንዘራለን፤ በሬዎቻችን ሞተዋል፤ ከሞት የተረፉትም በርካሽ ዋጋ ተሽጠዋል፤ ኋላ በምን ገዝተን እንዘራለን እያልን እየተጨነቅን ነው፤ ዙሪያው ገደል ነው የኾነብን፤ ካልተደረሰልን ተፋፍኖ መሞት ካልኾነ በስተቀር ሌላ አማራጭ የለንም” ነው ያሉን የከፋውን ድርቅ እና ያስከተለውን ችግር ሲገልጹልን፡፡

እኛን የገጠመን መከራ አይግጠማችሁ የሚሉት ጋሽ ጥጋቡ ወገን ሲኾን ይርዳን፣ ባይረዳን እንኳን ቀን ቢመልሰው፣ ቀን ሲወጣ የምንከፍለው በብድር ይሰጡን ነው ያሉት፡፡ ወገን ሁሉ አደጋ ላይ መኾናችን አይቶ እጁን ይዘርጋልን ሲሉም ተማጽነዋል፡፡

በዚሁ በጃናሞራ ወረዳ ባሕር አምባ የሚኖሩት ቄስ ዋኘው ባይነሳኝ “የክረምት ወግ ሳናይ አልፈን፤ እንደ ተዘራ የበቀለ ነገር የለም፤ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ነው ያለነው” ነው ያሉት፡፡ እንዲህ አይነት ዘር ያልበቀለበት፣ ልምላሜ ያልታየበት የከፋ ድርቅ እንኳን በእኛ ዘመን በቀደመው በአባቶቻችን ዘመን እንዳልደረሰ እና ሰምተውም እንደማያውቁ እድሜ ጠገብ አባቶች ነግረውናል ይላሉ፡፡

“የቀድሞው ድርቅ ዝናብ ጥሎ ባይኾን ለከብት የሚሆን ሣር ያበቅል ነበር፤ የአሁኑ ግን አስከፊ እና አሳዛኝ ነው፤ እኛ እንዲህ አይነት ድርቅ ሰምተንም አናውቅም” ይላሉ ቄስ ዋኘው አስከፊውን ድርቅ ሲገልጹት፡፡ ክረምት ባለመኖሩ ተስፋ ቆርጠን ከረምን ነው ያሉን፡፡ ደንግጠናል፤ የሚቀመስ ስለሌለ በእኛ አካባቢ የእንስሳት ዝርያ ይጠፋል ስጋት አለን፡፡ ሰውም በረሃብ መጎዳቱን እና እሞታለሁ በሚል ስጋት እየኖረ ነው ብለውናል፡፡

“ወንዞች ሙላት ሳያገኛቸው ስለከረመ አለቅት አፍርተው ከብቶቻችን ከረሃብ በላይ በአለቅት ተጎድተው ነበር፡፡ በቅርብ ዝናብ ዘንቦ ወንዞችን ጠረገልን፤ አለቅቱን አጠፋልን፤ ሰኔ ላይ የተዘራው ዘር አሁን በቀለ፡፡ ግን ምንም አይኾንም” ነው ያሉት፡፡ ካልተደገፍን እና ለእንስሳት መኖ ካልደረሰልን እንስሳቶቻችን ይጠፋሉ፤ እንስሳቶቻችን ከጠፉ ደግሞ ከመከራ ላይ መከራ ይደራረብብናል ብለውናል፡፡ መንግሥት እና ልበ ቀና ወገኖች የእለት ምግብ ይዘው ካልጠየቁን ሰው በረሃብ ያልቃል ይላሉ፡፡

የሰሜን ጎንደር ዞን አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሰላምይሁን ሙላት በጦርነት የቆዬ ዞን እንደነበር ያስታውሳሉ፤ ከጦርነቱ ጠባሳ ለማገገም ሥራዎችን እየሠሩ ባለበት ወቅት በተፈጠረው ድርቅ ማኅበራዊ እና ሥነ ልቡናዊ ጉዳት መድረሱን ነው የተናገሩት፡፡

እንደ ኀላፊው ገለጻ በዞኑ በሥድስት ወረዳ እና በ83 ቀበሌዎች ሙሉ ለሙሉ እና በከፊል ድርቅ ተከስቷል፡፡ ከ452 ሺህ በላይ ወገኖችንም በድርቅ ምክንያት ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ መኖ እና ውኃ ባለመኖሩ እንስሳትም በስፋት ሞተዋል፤ የምግብ እጥረት በመከሰቱ ተማሪዎች ለመማር ተቸግረዋል፤ ተላላፊ እና ሌሎች በሽታዎችንም እንዲከሰቱ በር ከፍቷል ነው ያሉት፡፡ ድርቅ የሚምረው እንደሌለም አንስተዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት ግብረ ኀይል ተቋቁሞ በማጥናት ወገኖች ከቀያቸው ሳይለቁ ባሉበት ለመደገፍ የሚያስችል ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ከጦርነት ያላገገመው ማኅበረሰብ ተጨማሪ ችግር መግጠሙን ያነሱት ኀላፊው የክልሉ፣ የፌዴራል መንግሥት እና ዪኒቨርሲቲዎች ጥናት ማድረጋቸውንም አንስተዋል፡፡ አስቸኳይ ድጋፍ ለማቅረብ እንዴት ይገኛል የሚለውን መለየታቸውን እና በጉዳዩ ላይ መወያዬታቸውን ነው የተናገሩት፤ ዪኒቨርሲቲዎች ድጋፍ አድርገዋል፤ የክልሉ መንግሥትም አስቸኳይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ድጋፍ ማድረጉን ነው ያነሱት፤ የፌዴራል መንግሥትም የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት ድጋፍ መፍቀዱን ነው የተናገሩት፡፡

የተጀመረው ድጋፍ ተስፋ ሰጪ መኾኑን የሚያነሱት ኀላፊው ከችግሩ አስከፊነት አንጻር ግን በቂ አይደለም ነው ያሉት፡፡ ድጋፉ እና ችግሩ የሚመጣጠን አለመኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የእንስሳት መኖ እና ውኃ ችግር ሰፊ መኾኑንም ተናግረዋል። በጤና፣ በትምህርት እና በሰበዓዊ እርዳታ ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግ እና ወገኖችን እንዲታደግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

መተባበር ከተቻለ እንስሳትንም ሰዎችንም ማትረፍ ይቻላል፤ ደጋግ ኢትዮጵያዊያን፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች እጃቸውን እንዲዘረጉም ጠይቀዋል፤ እስካሁን የነበረውን ችግር ሳይኾን ወደፊት ሊመጣ የሚችለውን በማሰብ መረባረብ ይገባል ነው ያሉት፡፡

የአማራ ክልል ርእሰ መስፈሥተዳደር አረጋ ከበደ ወገኖች በድርቅ ምክንያት እንዳይጎዱ ክልሉ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን መናገራቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የክልሉ መንግሥት በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣ የተሻለ ያመረቱ አርሶ አደሮች፣ ነጋዴዎች፣ የልማት ድርጅቶች እና መላው ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ እንዲያደርጉ መጠየቁም ይታወሳል፡፡

በችግር ያሉት ወገኖች ደራሽ ወገኖችን ይሻሉ፡፡ እኒያ ደጋግ ሰዎች በታሪክ እንደሚነገረው ሁሉ በሬዎቻችን አልቀው፣ ዘራቸው ሳይበቅል መክኖ ቀርቶ እንዳያልቁ ከእለት ጉርስ የተረፋቸው፣ ከዓመት ልብስ ተከፍሎ የሚሰጥ ያላቸው ሁሉ ይሰጧቸው፤ ከመከራ ያወጧቸው ዘንድ ይማጸናሉ፡፡

ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ በሠርክ የሚኖሩት፣ አንድ ቀን የሚያሳዩት”
Next articleየተለያዩ ሚስዮኖች 18ተኛውን የብሔር ፣ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል እያከበሩ ነው።