
ባሕር ዳር: ኅዳር 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሠርክ ይኖሩታል፤ ለዘመናት አጊጠውበታል፤ ለዘመናት ተውበውበታል፤ ተፈርተውበታል፤ ኮርተውበታል፤ ነጻነታቸውን ጠብቀውበታል፤ አንድ ኾነው በዓለም ታሪክ ገዝፈውበታል፤ በጠላቶቻቸው ፊት በግርማ ታይተውበታል፤ አሸናፊነትን ብቻ ያውቁበታል፡፡
ኩራትን ከደግነት፣ ጀግንነትን ከቅንነት፣ ጥንታዊነትን ከነጻነት ጋር አጣምረው ይዘዋል፡፡ በጠላቶቻቸው ፊት ገዝፈው ኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያ የሚሏት ሀገር፤ ኢትዮጵያዊነት የሚሉት ግብር አላቸው እና በዘመቱበት ሁሉ ያሸንፋሉ፤ በጨለማ ዘመን ብርሃን ኾነው ይሻገራሉ፤ መሻገሪያ በሌለበት ጊዜ የዘመን ድልድይ ሠርተው ያልፋሉ፡፡
ኢትዮጵያ የሚሏት ሀገር ኢትዮጵያዊነት የሚሉት ግብር ረቂቅ ነው ችለው የማይገፉት፣ ገፍተው የማይጥሉት፤ ተኩሰው የማይገድሉት፤ ታግለው የማያሸንፉት፡፡ አንድነትን፣ ፍቅርን፤ ከራስ በላይ ለሰው ማሰብን፣ ሰውነትን፣ መልካምነትን፣ ደግነትን፣ ጀግንነትን በሠርክ ይኖሩታል፤ በሠርክ ይታዩበታል፤ ከቀናት በአንዷ ቀን ደግሞ ከአራቱም ንፍቅ ተጠራርተው፣ በፍቅር እየተቃቀፉ አንድነታቸውን፣ ፍቅራቸውን፣ ጀግንታቸውን፣ ጥንታዊነታቸውን፣ ነጸነታቸውን፣ እሴታቸውን፣ ባሕላቸውን፣ ሃይማኖታቸውን ለዓለም ሁሉ ያሳዪበታል፡፡
ኢትዮጵያ የተባለች ሀገር፣ ኢትዮጵያዊ ይሉት ማንነት፣ ኢትዮጵያዊነት የተሰኘ ረቂቅ ምስጢር ከፍ ብሎ ኖሯል፤ በነጻነት ተከብሯል፡፡ በጠላቶች ተፈርቷል፡፡ በወዳጆች ተወዷል፡፡ ከባርነት መውጫ መንገድ፣ ከጨለማ ማለፊያ ብርሃን ኾኗል፡፡ ኢትዮጵያዊነት በቃል እንደሚናገሩት፣ በብዕር እንደሚጽፉት፣ በብራና እንደሚያሰፍሩት አይደለም፤ ኢትዮጵያዊነት ይሉት ምስጢር የማይሸነፍ ረቀቂ፣ የማይረታ ታላቅ ነገር ነውና፡፡
ኢትዮጵያዊ እና ኢትዮጵያዊነት መገለጫው ነጻነት፣ አንድነት፣ ኅብረት፣ ጥንታዊነት፣ ደግነት ነው፡፡
ንበሩ እድ ኤርምያስ ከበደ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት በሚለው መጽሐፋቸው ኢትዮጵያዊነት ሥጋዊነትን መንፈሳዊነት ላይ መሥርቶ የመኖርን ሥርዓት የሚያስቀድምና የሚያረጋግጥ ሕልውና ነው ይሉታል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከጥንት ጀምረው በሥጋ ዘር ብቻ ሳይኾን በመንፈስም ፍጹም እንድ ኾነው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ጠብቀው መኖር የቻሉት ተስማምተው በተቀበሏቸው ከአምላክ እውነት በመነጩት የውኅደት ኀይል ነው ይላሉ፡፡
ባለቅኔው ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን ደግሞ በቅኔያቸው ኢትዮጵያዊነት ይሉትን ታላቅ ነገር ሲገልጹ
“ኢትዮጵያዊነት ማተብ ነው በአካልና መንፈስ ጽናት
በአበው ታሪክ አምኖ መኩራት፡፡
ኢትዮያዊነት የዘለዓለም ኅብረት ሸማ
ዘረኝነትን አውድማ የምትወጣ ከጨለማ” ሲሉ ይገልጹታል፡፡ ኢትዮጵያዊያን በጥብቅ መሠረት ላይ በጸናች ሀገራቸው ለዘመናት ኖረዋል፡፡ ክፉና ደጉን፣ መከራና ተድላውን በጽናት አሳልፈዋል፡፡ እነሆ ዛሬም በተወደደች ሀገራቸው፣ በተከበረች ማንነታቸው እየኮሩ እና እየተከበሩ እየኖሩ ነው፡፡
ኢትዮጵያዊያን መከራ እንደሚስማር እያጠበቃቸው አያሌ የፈተና ዘመናትን አልፈዋል፡፡ እንደ ሀገር እና እንደ ሕዝብ እንዲጠፉ የታወጀባቸውን አዋጅ በአንድነታቸው ሽረዋል፡፡ የአንድነታቸው እና የኢትዮጵያዊነታቸው መሠረት የጸና ነው እና በመከራ አይሰበሩም፤ በጣለቶቻቸው አዋጅ አይደነብሩም፡፡
ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት የኖሩትን፣ እየኖሩት ያሉትን እውነት እና ማንነት ከቀናት በአንዷ ቀን የሚያከብሩባት ቀን ዛሬ ናት፡፡ ከአራቱም ንፍቅ ተሰባስበው በምሥራቅ ተገናኘተዋል፡፡ በምሥራቅ ተስፋና ብርሃን እንደሚወጣ ሁሉ እነርሱም በታላቅ ተስፋ ምሥራቅ ላይ ከትመዋል፡፡ ለዘመናት በጠበቁት ውበት እና ማንነት ደምቀዋል፡፡ በማይጠገብ ውበታቸው፣ ባልተበረዘ ባሕላቸው፣ በተጠበቀ ወግና ሥርዓታቸው በምሥራቅ ተሞሽረዋል፡፡ ምሥራቅ የብርሃን መውጫ፣ የተስፋ መምጫ፡፡
ኢትዮጵያዊያን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ማክበር ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህች ቀንም በአንድነት እና በደመቀ ውበት ለዓለም የሚታዩበት፣ ፍቅር የሚዘሩበት፣ ተስፋ እና ሰላም የሚሰብኩበት ነው፡፡ አንዳንዶች ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት የኖሩበትን እንደ አዲስ ማክበር ምን ይሠራላቸዋል? ምን አዲስ ነገር ያመጣላቸዋል? ለምን ቢሉ የሚኖሩት እውነት ነውና ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በሠርክ የሚኖሩትን እውነት እና ማንነት በአደባባይ ባወጡት ጊዜ የበለጠ ፍቅራቸውን፣ አንድነታቸውን፣ ተስፋቸውን ያጠነክራል እና የተገባ ነው ይላሉ፡፡ መከበሩ አንድነትን ከማጠናከር አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽዖ አለው ነገር ግን አከባበሩ ሕዝባዊ ሊኾን ይገባል፤ የፖለቲከኞች እና የፖለቲካ ማራመጀ በኾነ ጊዜ ግን ትክክለኛውን ዓላማ እንዳይመታ ያደርገዋል ነው የሚሉት፡፡
በወልድያ ዪኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ማብሬ ታዴ መሰባሰብ እና በአንድ ላይ በአንድ ሥፍራ መገኘት መልካም ነገር ነው ይላሉ። መምህሩ በዓሉን በደንብ ተጠቅመንበታል ወይ? ሲሉም ይጠይቃሉ። ከፖለቲካ ዘመቻ ያለፈ ሕዝባዊ የኾነ፣ ከወገንተኝነት ነጻ በኾነ መንገድ ተከብሯል ወይ የሚለውን መጠየቅ መልካም ይኾናል እንጂ በዓሉን በትክክለኛው መንገድ መጠቀም ከተቻለ ጠቀሜታው የላቀ ነው ይላሉ፡፡
በዓሉን ሕዝባዊ ማድረግ የተገባ ነው፣ ጅምሩም ጥሩ ነው ይላሉ፡፡
የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መልከ ብዙ ፋይዳ ያለው፤ ብዝኃነትን ላቀፈች ሀገር አንድነትን የሚያጠናክር፣ በአራቱም ማዕዘን የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የሚያስተዋውቅ መኾኑንም ይገልጻሉ፡፡ አንዱ የአንዱን በዓል እንዲቀበል፣ አንደኛው የአንደኛውን እንዲያከብር ያደርጋል፡፡ ማኅበረሰብን ከማኅበረሰብ የሚያገናኝ ሁነት ያስፈልጋል የሚሉት መምህሩ የብሔር ብሔረሰቦች ቀንም ማኅበረሰብን ከማኅበረሰብ ለማስተዋወቅ እና አንድነትን ለማጠናከር ይረዳል ነው የሚሉት፡፡
ሕዝባዊ በማድረግ በዓሉ እንዲከበር ማድረግ ከተቻለ በሀገር ላይ በርካታ ለውጦችን ያመጣልም ይላሉ፡፡ እንደ ፖለቲካ መምህሩ ገለጻ በዓሉ በማኀበረሰቡ ዘንድ የኔነት ስሜት እንዲፈጠርበት፣ ከየትኛው አይነት የፖለቲካ ትርጓሜ ነጻ በማድረግ ሕዝቡ እንዲያከብረው ማድረግ ከተቻለ ፋይዳው ብዙ ነው፤ ጠለቅ ያለ ነው፤ ትርጉም አለው፤ የሀገሪቱን አንድነት ከፍ በማድረግ ሂደት ውስጥ ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡
ለሀገር የትውልድ አደራ እና እርሾ ያስፈልጋል፤ የጋራ የኾነ ታሪክ፣ እሴት ያሻል፤ ሀገር የሚገነባው በጋራ በኾነ መሠረት ላይ ነውም ይላሉ መምህሩ፡፡ ኢትዮጵያዊያን የነበራቸው የቆዬ የአንድነት እርሾ እንደ ሀገር አቆይቶናል፤ እንደ ሕዝብ አስከብሮን ኖሯል ነው ያሉት፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ያጠናክራል፤ አንድነትን ከፍ ያደርጋል፤ ፍቅርን ያደረጃል፤ ሰላምን ያጸናል፤ ልብ ለልብ ያስተዋውቃል፤ በአንዲት ሀገር ፣ በአንዲት ሠንደቅ ለማሰባሰብ እና ለማኩራት ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡ ኢትዮጵያን ያጸናት እና ያቆያት አንድነት ነው፡፡ አንድነት የኢትዮጵያ መሠረት ነውና፡፡
ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን “አባቶቻችን አብረው መኖር ስለሚያውቁ ነው የሺህ ዘመናት ታሪክ ያላት ሀገር ያቆዩን፡፡ የእኔ ዘር ከአንተ ይበልጣል፤ የሰይጣን ጨዋታ ቢቀር ይሻላል፡፡ ማንም ከማንም አይበልጥም፡፡ የእኔ ጎሳ ከአንተ ይበልጣል ማለት የመጨረሻ ጅልነት ነው” ይላሉ፡፡ አንድነት፣ እኩልነት የኢትዮጵያዊያን መገለጫ ነው፡፡ መለያዬት መጠላለፍ የኢትዮጵያዊያን አባቶች መገለጫ እና ማንነት አይደለም፡፡ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያዊያን የግብር መገለጫ የሚኾነው አንድነት፣ ነጻነት እና ጽናት ናቸው፡፡
ደጋጎቹ ከየአቅጣጫው ተጠራርተው ምሥራቅ ላይ ከትመዋል፡፡ በፍቅር ተሰባስበዋል፡፡ በአንድት የከበረች ሠንደቅ ሥር ተጠልለዋል፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያዊያን ውበታቸውን የሚገልጹበት፣ ብዙ ኾነው ሳለ እንደ አንድ የሚታዩበት ቀን ናት፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!