
ባሕር ዳር: ኅዳር 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ዞን ኮማንድ ፖስት በማንኩሳ ከተማ ከወጣቶች ጋር በሰላምና ጸጥታ ዙርያ ውይይት አካሂዷል።
ውይይቱን የመሩት የኮሩ የሠራዊት ሥነ-ልቡና ግንባታ ቡድን መሪ ሌተናል ኮሎኔል ምሥራቅ መንበር አሁን የተፈጠረውን የሰላም መደፍረስ ሠርተው መለወጥ ያለባቸውን ወጣቶች የሚጎዳ ነው ብለዋል።
ከዚህ ችግር ለመውጣት ወጣቶች ከመንግሥት የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት እና በባለቤትነት ስሜት በመንቀሳቀስ አካባቢያቸውን ነቅተው መጠበቅ እንዳለባቸውም ሌተናል ኮሎኔል ምሥራቅ አስገንዝበዋል።
የጃቢ ጠሕናን ወረዳ አሥተዳዳሪ አቶ ዓላምረው ሹመቴ በወረዳው ችግር እንዳይከሰት ሁሉም አስፈላጊውን ሥራ መሥራት እንዳለበት ተናግረዋል። የሕዝብ ጥያቄዎች እንዳሉ ይታወቃል፤ በተረጋጋ እና በሠለጠነ አግባብ ምላሽ እንዲያገኙ መታገል እንጂ ነፍጥ በማንገብ እና በጦርነት የሚመጣ መፍትሔ ግን አይኖርም ብለዋል።
ወጣቶችም ይህንን በመረዳት ከጸጥታ አካላት ጋር ተባብረው አካባቢያቸውን በመጠበቅ ከጥፋት መራቅ እንዳለባቸውም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት የማኅበራዊ ድረ ገጽ መረጃ እንደሚያመላክተው በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ወጣቶች ሰላም ማጣት በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድር መኾኑን ገልጸዋል።
ሰላም እንዲመጣ ሁሉም ወጣቶች ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ጋር መሥራት እንዳለባቸው ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!