
ደብረ ብርሃን: ኅዳር 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል ቀጣይነት ያለው ግንዛቤ እና ሕጋዊ ተጠያቂነት ሊዳብር እንደሚገባ ተጠቁሟል።
“መቼም የትም በምንም ሁኔታ ፆታዊ ጥቃትን ዝም አንበል” በሚል መሪ መልእክት እየተከበረ የሚገኘው ዓለም ዓቀፍ የፀረ ፆታዊ ጥቃት (የነጭ ሪቫን) ቀን ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እንዲቆሙ የሚያሳስብ ነው።
የሰሜን ሸዋ ዞን ሴቶች፣ ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ከተባባሪ አካላት ጋር በመኾን ከሰባት የወረዳ እና ከተማ አሥተዳደሮች የተውጣጡ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት በዓሉን አክብሯል።
አሚኮ ያነጋገራቸው ተሳታፊዎች እንዳሉት ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመከላከል የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎችን ከማከናወን በተጨማሪ ጥቃቱን በሚፈጽሙ አካላት ላይ ከፍትህ ተቋማት ጋር በመኾን አስተማሪ እና ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ እየተደረገ እንደኾነ ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ዘርፈ ብዙ ፆታዊ ጥቃት ለመከላከል አሁንም ቢኾን በቂ የኾነ መረጃ እና ማስረጃ በማግኘት በኩል ሰፊ ክፍተቶች መኖራቸውን ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የተናገሩት።
የመምሪያው ኀላፊ የሮምነሽ ጋሻውጠና በበኩላቸው ፆታዊ ጥቃቶችን ለመከላከል ለማኅበረሰቡ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑን ጠቅሰው ከወቅታዊ የፀጥታ ችግሮች አንፃር ግን ተደራሽ ለማድረግ አለመቻሉን ነው የተናገሩት።
ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመከላከል መምሪያው ከፍትሕ አካላት ጋር አየሠራ መኾኑን ጠቅሰው ጥቃት አድራሾች ላይ የሚቀርቡ መረጃዎች እና ማስረጃዎች ውስን በመኾናቸው አስተማሪ እና ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ውስንነት መኖሩን ተናግረዋል። ለዚህም ማኀበረሰቡ ተባባሪ መኾን እንዳለበት ነው መምሪያ ኀላፊዋ ያሳሰቡት።
ዓለም ዓቀፍ የፀረ ፆታዊ ጥቃት ቀን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለ32ኛ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ18ኛ ጊዜ ከኅዳር/2016 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ መኾኑን ከመምሪያው ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ዘጋቢ፦ በላይ ተስፋየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!