የኅብረተሰቡን ጤና ለማሻሻል የላብራቶሪ ምርመራ ጥራት እና ተደራሽነት በትብብር ማሳደግ እንደሚገባ ተጠየቀ።

38

ባሕር ዳር: ኅዳር 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሁለተኛው የጤና ላብራቶሪ ፌስቲባል በባሕር ዳር ተካሂዷል።

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ እንዳሉት የጤና ተቋማት ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለማኅበረሰብ እንዲሰጡ ዘመናዊ የላብራቶሪ ግብዓቶችን ተደራሽ ማድረግ የኢንስቲትዩቱ ቀዳሚ ተግባር ነው።

ኢንስቲትዩቱ ሥራ ከጀመረ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ የሕክምና ሥርዓቱን ለማዘመን የላብራቶሪ አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ እና ለባለሙያ ሥልጠናዎችን እየሰጠ ነው። የወረርሽኝ ልየታ እና ክትትል፣ የጥናት እና ምርምር ሥራም እየሠራ ይገኛል።

ይሁን እንጅ የላብራቶሪ አገልግሎቱን በጥራት እና በፍጥነት ለመሥጠት ውስንነቶች አሉ ተብሏል። የግብዓት መቆራረጥ፣ ተከታታይነት ያለው የሰው ኃይል ሥልጠና አለመኖር፣ የላብራቶሪ መረጃዎችን ማዘመን የሚያስችል መሠረተ ልማት አለመኖር እና ወቅቱ የሚጠይቀውን አጠቃላይ የላብራቶሪ አገልግሎት መሠረተ ያደረገ ንቃተ ጤና በሚፈለገው ደረጃ አለማደግ መሠረታዊ ችግሮች እንደኾኑ ተነስቷል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አቶ አብዱልከሪም መንግሥቱ የጤና ተቋማትን የላብራቶሪ አገልግሎት ለማሻሻል በ2009 ዓ.ም የላብራቶሪ አገልግሎት መመሪያ በማውጣት በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል። የጤና ተቋማትን የላብራቶሪ ምርመራ ለማሳደግ የባለሙያውን አቅም ማሳደግ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ እንደሚገም ኀላፊው ገልጸዋል።

ፍትሐዊ እና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለመስጠት ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየካናዳ ሐኪሞች እርዳታ እና ድጋፍ ማኅበር የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
Next articleበሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል ቀጣይነት ያለው ግንዛቤ ፈጠራ እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ።