
አዲስ አበባ: ኅዳር 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የካናዳ ሐኪሞች እርዳታ እና ድጋፍ ማኅበር ለአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ግምታቸው 15 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ገልጿል።
ድጋፉን የካናዳ ሐኪሞች ልማት እና እርዳታ ድርጅት ካንትሪ ማኔጀር ዓባይነሽ አየለ ለአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ተወካዮች አስረክበዋል።
ማኅበሩ ከካናዳ መንግሥት በተገኘ 15 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ ለአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ድጋፍ አድርጓል።
ካንትሪ ማኔጀሯ ማኅበሩ ለ11 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች የሥነ ተዋልዶ ሥልጠና እና የንጽሕና መጠበቂያ ቁስ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል።
ለ40 ዓመታት ያክል በአማራ፣ ኦሮሚያ እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በጤናው ዘርፍ ሲያገለግል የቆየ ማኅበር እንደኾነም ገልጸዋል።
የካናዳ ሐኪሞች እርዳታ እና ድጋፍ ማኅበር ፕሮጀክት ማኔጀር ሳንድራ አበጀ እንደገለጹት ማኅበሩ በኢትዮጵያ በነበረው ቆይታ በጤናው ዘርፍ በርካታ ሥራዎች ሲሠራ ቆይቷል።
ወደ ጤናው ዘርፍ ከመግባቱ በፊት በተለይም በሰሜን ሸዋ በችግር ጊዜ አፈታት እና በንጹህ መጠጥ ውኃ ለሀገሪቱ ብዙ አበርክቷል ብለዋል።
በሥነ ተዋልዶ ጤና ወጣቶች ተጠቃሚ እንዲኾኑም ሥልጠናዎች ሲሰጥ መቆየቱን የካናዳ ሐኪሞች እርዳታና ድጋፍ ማኅበር ፕሮጀክት ማኔጀሯ ገልጸዋል።
ድጋፍ የተደረጉት እቃዎች በአማራ ክልል ለማዕከላዊ ጎንደር እና ኦሮሚያ ክልል ለአርሲ ዞን 11 ሆስፒታሎች የሚውል ነው ተብሏል።
ዘጋቢ፦ አየለ መስፍን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!