
ደብረ ብርሃን: ኅዳር 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)አድህኖ የተቀናጀ የገጠር ልማት ማኅበር በሰሜን ሸዋ ዞን ባለፉት 22 ዓመታት በአከባቢ ጥበቃ ላይ ዋና ትኩረቱን አድርጎ እየሠራ ይገኛል። ማኅበሩ ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት በዞኑ ከፍተኛ ውጤት ለሚያስመዘግቡ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ሽልማት እና ድጋፍ እያደረገ ይገኛል::
“የሰሜን ሸዋ ብሩህ አዕምሮ ሽልማት” የተሰኘው ይህ ፕሮጀክት ማኀበሩ አሜሪካን ሀገር ካሊፎርንያ ከሚገኘው ብሩህ አዕምሮ ከተሰኘ ማኅበር እና አቶ እያቄም ወልደሃና ከተባሉ ለጋሽ ግለሰብ በሚያገኘው ድጋፍ የሚተገበር ፕሮጀክት ነው::
ፕሮጀክቱ በ2015 ዓ.ም የተጀመረ ነው ያሉን የማኅበሩ ዳይሬክተር ዮናታል ፍቅሬ ፕሮጀክቱ ለ20 ዓመት የሚቀጥል ስለመኾኑም ተናግረዋል::
በየዓመቱ በዞኑ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገቡ ሰባት ተማሪዎች በፕሮጀክቱ ይታቀፋሉ ያሉት አቶ ዮናታል ለአምስት ዓመታት የቁሳቁስ እና የገንዘብ ድጋፍ ይደረግላቸዋል ብለዋል::አልባሳት፣ ላብቶፕ፣ የትራንስፖርት ወጭ እና ወርሃዊ የገንዘብ ድጋፍ በፕሮጀክቱ በየዓመቱ ለሚታቀፉ ሰባት ተማሪዎች የሚሠጡ ድጋፎች ናቸው::ለሰባት ተማሪዎች በዓመት 21 ሺህ ዶላር ስሌት መሠረት ፕሮጀክቱ በየዓመቱ ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡ ጎበዝ ተማሪዎችን እየደገፈ የሚቀጥል ይኾናል::
ከፍተኛ ውጤት አምጥተው በፕሮጀክቱ የታቀፉ ተማሪዎች ባገኙት እድል መደሰታቸውን ገልጸዋል። በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የላቀ ውጤትን ለማስመዝገብ እንደሚተጉ እና ማኅበሩም ኾነ ድጋፉን የሚያደርጉላቸው አካላት እና ሀገር የምትጠብቅባቸውን አደራ ለመወጣት እንደሚተጉ ቃል ገብተዋል::
የፕሮጀክቱ ዓላማ ተማሪዎቹ በ12ኛ ክፍል ያስመዘገቡትን ውጤት በከፍተኛ ትምህርት ተቋምም እንዲያስቀጥሉ ለማስቻል እና ምጣኔ ሃብታዊ ችግር ያለባቸውን የተማሪ ወላጆች ለመደገፍ ስለመኾኑም ገልጸዋል::
የ2ኛው ዙር የሰሜን ሸዋ ብሩህ አዕምሮ ሽልማት ሥነ ሥርዓት ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች፣ የተማሪ ወላጆች፣ ርዕሰ መምህራን የትምህርት መምሪያ አመራሮች እና ባለሙያዎች በተገኙበት በደብረ ብርሃን ከተማ ተከናውኗል::
ዘጋቢ:- ሥነጊዮርጊስ ከበደ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!