“በወጣቶች ማኅበራዊ ተሳትፎ እና በስፖርቱ ዘርፍ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል” የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ

56

ደሴ: ኅዳር 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ የ2015 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም፣ የ2016 በጀት ዓመት እቅድ እና የበጀት ዓመቱ አንደኛ ሩብ ዓመት አፈፃፀምን በኮምቦልቻ ከተማ እየገመገመ ነው።
የቢሮው ምክትል ቢሮ ኀላፊ ተሾመ ፈንታው በክረምት እና በበጋ በጎ ፈቀድ ሥራ በስፖርቱ ዘርፍ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።

በበጎ ፈቃድ ሥራው በደም ልገሳ፣ በሱስ የተጠቁ ከደባል ሱስ እንዲላቀቁ በማድረግ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት በመገንባት የክልሉ ወጣቶች ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በስፖርቱ ዘርፍ ደግሞ ሕዝባዊ አደረጃጀቶችን በማጠናከር በክልሉ የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮችን በስኬት ማጠናቀቅ ተችሏል ነው ያሉት።

ለአብነት የመላ አማራ ጨዋታዎች፣ የክለቦች ሻምፒዮና፣ የመሥሪያ ቤት ሠራተኞች ውድድሮች በስኬት ተከናውነዋል። ለብሔራዊ ቡድንም ስፖርተኞችን ማስመረጥ ተችሏል ብለዋል። በክልሉ የገጠመው የሰላም መደፍረስ በቢሮው የእቅድ አፈጻጸም ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩንም ተናግረዋል።

የዞን ወጣቶች እና የስፖርት መምሪያ ተወካዮች በበኩላቸው አንፃራዊ ሰላም በነበረባቸው ከተሞች እና ወረዳዎች በክረምት በጎ ፈቃድ በርካታ ወጣቶችን በማሳተፍ የተለያዩ ሥራዎች ማከናወን እንደቻሉ አስረድተዋል።

በ2016 በጀት ዓመት ቀሪ ጊዜያት በተለይ ወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዲኾኑ በትኩረት እንደሚሠራ የቢሮው ምክትል ቢሮ ኀላፊ ተሾመ ፈንታው ተናግረዋል። በግምገማ መድረኩ የምሥራቅ አማራ ዞኖች፣ ከተማ አሥተዳደሮች፣ የወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊዎች እንዲሁም ተወካዮች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፦ ከድር አሊ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል 13 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ መሰብሰቡን የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።
Next article“እንኳን ለኢትዮጵያዊነት በዓል አደረሳችሁ” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ