
ባሕር ዳር: ኅዳር 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሙስና ወንጀልን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የሕዝቡ ትብብርና እገዛ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል።
የሙስና ወንጀልን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የሕዝቡ ትብብርና እገዛ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የብሔራዊ ጸረ ሙስና ኮሚቴ ጥሪ አቅርቧል።
ለተከታታይ ቀናት በተለያዩ መርሐ ግብሮች “ሙስና የጋራ ጠላታችን ነው፣ በኅብረት እንታገል” በሚል መሪ ሃሳብ የተከበረው 20ኛው የፀረ-ሙስና ቀን የማጠቃለያ መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል እና የብሔራዊ ጸረ ሙስና ኮሚቴ ሰብሳቢ ተመሥገን ጥሩነህ፤ ሙስና የሕዝብ ብሎም የሀገር ጠላት በመኾኑ የጋራ ትግል ማድረግን ይጠይቃል ብለዋል።
በመሆኑም የሙስና ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ብሔራዊ ጸረ ሙስና ኮሚቴ ተቋቁሞ ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል። የሙስና ወንጀልን መከላከል በተወሰነ አካል ብቻ የሚሳካ ባለመኾኑ የሕዝቡ እገዛና ጥረት ወሳኝ መኾኑን ተናግረዋል።
የሕዝብን ጥቆማ መነሻ በማድረግ በሙስና ወንጀል የተያዙ 146 ተከሳሾች በሕግ ተጠያቂ ኾነው የጥፋተኝነት ውሳኔ እንደተላለፈባቸው ጠቁመዋል በተጨማሪም በርካታ የመንግሥትና የሕዝብ ሃብቶች ከመዝባሪዎች ተመላሽ እንዲኾኑ መደረጉንም ተናግረዋል።
ሙስናን በመከላከል ሂደት በእስካሁኑ ሂደት ጥቆማና መረጃዎችን በመስጠት ሕዝቡ ላደረገው አስተዋጽኦ አመስግነው በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። ኢዜአ እንደዘገበው በቀጣይ በተለይም የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ግልጽ አሠራር በመዘርጋት ሌብነትና ብልሹ አሠራሮችን ሊከላከሉ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!