
ባሕር ዳር: ኅዳር 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች ማኅበር የሴቶችን ጥቃት ለመከላከል የዓለም አቀፉን የፀረ ፆታዊ ጥቃት መሠረት አድርጎ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተወያየ ነው።
ማኅበሩ በየዓመቱ ከሕዳር 15 እስከ ሕዳር 30 ድረስ የነጭ ሪቫን ቀንን ያከብራል፤ በዚህ ዓመትም በዓሉ በልዩ ልዩ ፕሮግራሞች ሲከበር ቆይቷል። ዘንድሮም ለ18ኛ ጊዜ “መቸም የትም በምንም ኹኔታ ጾታዊ ጥቃትን ዝም አንበል” በሚል መልእክት እየተከበረ ነው። ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል ማኅበረሰቡ ተሳታፊ መኾን እንዳለበት በበዓሉ ላይ ተመላክቷል።
የአማራ ክልል ሴቶች ማኅበር የቦርድ ሠብሳቢ ዳርእስከዳር ጌቴ በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል። ማኅበረሰቡ ለችግሩ ትኩረት ሠጥቶ መረጃ በመስጠት ችግሩ እንዳይፈጠር መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል። ወይዘሮ ዳርእስከዳር የሴቶችን ፆታዊ ጥቃት ለመከላከል የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል።
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ አብርሃም ጎሽም ከፆታዊ ጥቃት ጋር በተገናኘ በርካታ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው ገልጸዋል። በየጊዜው ለሚደርስ ፆታዊ ጥቃት የተሠጠው ክብደት እያነሰ እንደሄደም አንስተዋል።
ችግሮች ሲፈጠሩ የፍትሕ አካላት ቅንጅታዊ ሥራዎችን በመሥራት ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ተግባር እንዲፈጽሙም ጠይቀዋል።
እንደ ጎርጎሳውያሉ የዘመን ቀመር በ2013 የተደረገው ዓለም አቀፉ ጥናት ከ100 ሴቶች መካከል 35 ሴቶች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ፆታዊ ጥቃት እንደሚደርስባቸው አመላክቷል። በኢትዮጵያም ከሦስት ሴቶች አንድ ሴት ፆታዊ ጥቃት እንደሚደርስባት በውይይቱ ላይ በቀረበው የመወያያ ጽሑፍ ላይ ተመላክቷል።
ለጥቃቱ የወንዶች የበላይነት መኖር፣ የሕግ ሥርዓቱ መላላት፣ የማኅበረሰቡ ግንዛቤ አናሳ መኾን፣ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ክስተቶች በዋናነት ይጠቀሳሉ። በውይይቱ ላይ የሚመለከታቸው አካላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!