በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘችው ኳስ

89

ባሕር ዳር: ኅዳር 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከጨዋታ ውጪ የኾነ ውሳኔን የምታግዝ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ውጤት የኾነች ኳስ በሚቀጥለው ዓመት በጀርመን በሚደረገው የአውሮፓ ዋንጫ በጥቅም ላይ እንደሚውል የአውሮፓ እግር ኳስ አሥተዳዳሪ አካል እና አዲዳስ ይፋ አድርገዋል።

አዲዳስ በተባለው የስፖርት ግብዓት አምራች ድርጅት የተመረተችው ኳስ በጀርመንኛ “ፉስቦልሊቤ” የሚል ስያሜ ተሰጥቷታል፡፡ “የእግር ኳስ ፍቅር” ማለት ነው፡፡

“ፉስቦልሊቤ” (አዲሷ ኳስ) በውስጧ ጋይሮ ስኮፕ የተሰኘ መሳሪያ ተገጥሞላታል፡፡ ይህ ጋይሮ ስኮፕ በሰከንድ 500 ያህል የኳስ ንክኪ መረጃዎችን መላክ ይችላል።

ጋይሮ ስኮፕ ማለት በፍጥነት የሚሄድን ነገር በብርሃን ጨረር የነገሩን አቅጣጫ ለመለየት የሚያገለግል መሳሪያ ነው። ጋይሮስኮፕ የባለስቲክ ሚሳኤሎችን እና የሳተላይቶችን አቅጣጫ ፍንትው አድርጎ የሚያሣይ ቁስ መኾኑን ልብ ይሏል፡፡

በጋይሮስኮፑ አማካኝነት ከፉስቦልሊቤ ኳስ ጋር ንክኪ ያደረጉ የተጫዋችን እንቅስቃሴ የሚያሳይ የ3D ምስሎችን በጥራት የሚያሳዩ ደቂቅ ካሜራዎችም ተገጥመውላታል፡፡ በመኾኑም ወደ ኳሷ የሚጠጋው ተጫዋች ከጨዋታ ውጪ ከኾነ ጨዋታውን በኮምፒዩተር ለሚከታተሉት ባለሙያዎች ምልክት ታሳያለች ፡፡

እንደአሶሼትድ ፕረስ ዘገባ ይህ የዘመነ የኳስ ቴክኖሎጂ በ2024 የአውሮፓ ዋንጫም ተግባራዊ የሚደረገውን የቪዲዮ ረዳት ዳኝነት የውሳኔ አሰጣጥ ሂደትን በእጅጉ ይረዳል ነው የተባለው፡፡

“ፉስቦልሊቤ” ኳስ በሚቀጥለው ዓመት ከሰኔ 14 እስከ ሐምሌ 14/2024 በ51 ጨዋታዎች ጥቅም ላይ እንደምትውል የአውሮፓ እግር ኳስ አሥተዳዳሪ አካል እና አዲዳስ ከሰሞኑ በበርሊን ይፋ አድርገዋል፡፡

ዘጋቢ:- በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየብሔር ብሔረሰቦች በዓል ዝግጅት ላይ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ትልቅ እንደነበር የሱማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ሙስጠፋ ሙሐመድ ተናገሩ።
Next articleየሴቶችን ፆታዊ ጥቃት ለመከላከል ፍትሕ አካላት ቅንጅታዊ ሥራዎችን በመሥራት ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ተግባር እንዲፈጽሙ ተጠየቀ።