
ጅግጅጋ: ኅዳር 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል የሚከበርበት የሱማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ሙስጠፋ ሙሐመድ ስለበዓሉ አከባበር እና ዝግጅት መግለጫ ሰጥተዋል።
ፕሬዚዳንቱ በመግለጫቸው የብሔር ብሔረሰቦችን በዓል ለ2ኛ ጊዜ ለማዘጋጀት እድል ማግኘታቸውን ገልጸው እንግዶችን በተሻለ ደረጃ ለመቀበል ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ይህ በዓል ለክልሉ ሕዝቦች የተለየ ነው፤ ምክንያቱም አሁን ላይ የሕዝባችን ሰላም ተመልሶ ፊታቸውን ወደ ልማት ባዞሩበት ቀን መከበሩ ነው ብለዋል።
የበዓሉ ዝግጅት ሥራዎችን በተለይ የመሠረተ ልማት ሥራን በፍጥነት ማጠናቀቅ እንደሚቻል የታየበት እንደኾነ አስረድተዋል።
ክልሉ ሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮችን ማስተናገድ እንደሚችል ልምድ የወሰደበት እንደኾነም ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንቱ የብሔር ብሔረሰቦች በዓል በሁሉም ትብብር የሚሠራ በመኾኑ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ትልቅ እንደነበርም ተናግረዋል።
ከለውጡ በኋላ ብዙ ሥራዎች እንደተሠሩ ፕሬዚዳንቱ አብራርተዋል። በተለይ በትምህርት፣ በጤና እና በመንገድ መሠረተ ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ተሠርቷል ነው ያሉት።
ወደ ልማት ፊታችንን ስላዞርን በክልሉ ለማልማት ለሚመጡ አልሚዎች በራችን ክፍት ነው፤ ለዚህም መሰረታዊ የኾነው ሰላም እና ደኅንነት የተረጋገጠ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
በጅግጅጋ ለሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ለመጡ እንግዶች ጅግጅጋ ምቹ ኹኔታዎች እንደፈጠረችላቸው ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ አብነት እስከዚያ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!