
አዲስ አበባ: ኅዳር 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኅብረት ሥራ ማኅበራት መንግሥት ለወጠናቸው የልማት ስትራቴጅዎች አጋዥ ኾነው እየሠሩ መኾኑ ተገልጿል።
“የቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበራት አባላት እርስ በርስ ይደጋገፋሉ” በሚል መሪ ቃል የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ቀን በአዲስ አበባ እየተከበረ ነው። ቀኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ75ተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ2ኛ ጊዜ ነው የሚከበረው።
የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌታቸው መለሰ (ዶ.ር) ኅብረት ሥራ ማኅበራት መንግሥት ለወጠናቸው የልማት ስትራቴጂዎች አጋዥ ናቸው ብለዋል። ኅብረት ሥራ ማኅበራት ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ የብድር እና የቁጠባ አገልግሎትን ከገጠር ቀበሌዎች እስከ ከተማ ድረስ በማስፋት የኅብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮችን በመፍታት ላይ ይገኛሉ ሲሉም ገልጸዋል።
በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ.ር) ኅብረት ሥራ ማኅበራት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ የግብርና እቃዎችን በማቅረብ እና ለግብርና ምርቶች ገበያ በማመቻቸት ጉልህ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ቤቴል መኮንን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
