
ባሕር ዳር: ኅዳር 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የመከላከያ ሠራዊቱን እንደ ዓይኑ ብሌን ሌት ተቀን ነቅቶ ከሚጠብቀው ከአብራኩ ከወጣበት ሕዝብ ለመነጠል የሚደረገው ግብግብ በምንም መለኪያ ተቀባይነት አይኖረውም ብሏል የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ።
የቢሮው ሙሉ መልእክት ቀጥሎ ይቀርባል። ሀገር እንደ ሀገር ጸንታ ዳር ድንበሯ እና ሉኣላዊነቷ ተከብሮ ሕዝቦቿና ሃብታቸዉ ከማንኛውም ጠላት ተጠብቆ እንዲኖር አንድ ወጥ የኾነ የመከላከያ ኀይል ያስፈልጋታል፡፡ ለዚህም ነዉ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን እንደ ዓይናቸዉ ብሌን የሚሳሱለት ዘመናትን የተሻገረ ግዙፍ የመከላከያ ተቋም የገነቡት።
በሀገር ህልውና ላይ በውጭም ኾነ በውስጥ በሚገኙ ጠላቶች በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚቃጡ ጦርነቶችንም ኾነ የተለያዩ ትንኮሳዎችን መመከት የሚቻለው በሀገር መከላከያ ኀይል ነው፡፡ በአንድ ሀገር የሕግ የበላይነት ተከብሮ ሕዝብ በሰላም ወጥቶ በሰላም ለመግባት የሚችለው እና ማንኛውንም ሥራ ያለምንም ስጋት በነፃነት ማከናወን እንዲችልና ሠርቶ ለመለወጥ ሰላም ያስፈልገዋል፡፡ ለዚህ ሰላም መስፈን ደግሞ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ድርሻው ይህ ነው የማይባል በጥቂቱ ሊተመን የማይችል ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ እንደማንኛውም ሉአላዊ ሀገር የራሷ የኾነ ሁሌም የምትተማመንበትና የምትኮራበት የመከላከያ ኀይል አላት፡፡ ይህም ኀይል ጠላት እንደሚናገረው ከአንድ ወገን ብቻ የተዋቀረ ወይም የአንድ ብሔር ስብስብ አሊያም የአንድ የፖለቲካ ፓርቲን ጥቅም አስጠባቂ ብቻ ሳይኾን በሀገሪቱ ከሚገኙ ሁሉም ብሔር፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተውጣጣ ከአንዲት ኢትዮጵያ ማህፀን ተፀንሶ ለሀገር ሰላምና ሉአላዊነት ክብር የተወለደ ነው፡፡
ሠራዊታችን ሰላም አብሳሪ፤ ሀገርና ሕዝብን ጠባቂ፤ ዘመን የማይሽረው ፤ጊዜ የማይለውጠው፤ ሀገራችንና ሕዝቦቿን ከውጭም ኾነ ከውስጥ የሚቃጣባትን ጥቃት የሚመክት የሕዝብ ልጅ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዓለም የደረሰበትን ቴክኖሎጅ የተጎናጸፈ፣ ለሀገር ሉላዊነት ዘብ የቆመ፣ ሀገር ድንበሯ ተነካ፤ ሀገር ተደፈረች ሲባል በብርሀን ፍጥነት የሚደርስ ብሔር የለሽ የሕዝብ አለኝታ የኾነ፤ ከውስጥ የሚነሱ ግጭቶችን ከማብረድና ከማስታገስ እስከ ውጭ የሰላም ማስከበር ተልእኮው ድረስ የተዋጣለት ለመኾኑ አይደለም ወዳጅ ጠላቶች የሚመሰክሩለት ሃቅ ነው፡፡
ኾኖም የሀገራችን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዳር እስከዳር ላለው መላው የሀገሪቱ ሕዝብ ሰላምን ለማስጠበቅ ዋልታና ማገር ኾኖ እያገለገለ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ባልተለመደ መልኩ መከላከያ ሠራዊቱን አቅም እንደሌለው፤ የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ጠባቂና ተልእኮ ፈፃሚ እና ከአንድ ወገን ወይም ብሔር ብቻ የወጣ አድርጎ የመመልከት እሳቤ በግልም ኾነ በህቡዕ በማወቅም ኾነ ባለማወቅ እየተንጸባረቀና እየተነገረ መኾኑ የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡
ይህ ለሠራዊታችን የተሰጠ የዳቦ ስም መኾኑን የተረዱት ኢትዮጵያ ኢትዮጵያዊያን ለህልውናቸው ሲል እየተዋደቀ ለሚገኘዉ የመከላከያ ሠራዊት አጋር በመኾን እያከሸፉትና ሠራዊቱ በአንዲት ኢትዮጵያ ስም የቆመ መኾኑን አሳይተዋል እያሳዩም ይገኛሉ።
ስለኾነም የሁሉም በሁሉም የኾነውን የሀገር መከላከያ ሠራዊትን የአንድ ወገን ብቻ አድርጎ ማየት ሀገርን እንደመካድ የሚቆጠር በመኾኑ፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊቱን ከአንድ ወገን ወይም ብሔር የወጣ፤ የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ጠባቂና ተልእኮ ፈፃሚ እንዲሁም በሀገር ውስጥ ከሚገኙ አሊያም በውጭ ጠላት የሚሸነፍ አቅም ያነሰው አድርጎ የማየት አባዜ አግባብነት የሌለውና የመከላከያ ሠራዊቱን እንደ ዓይኑ ብሌን ሌት ተቀን ነቅቶ ከሚጠብቀው ከአብራኩ ከወጣበት ሕዝብ ለመነጠል የሚደረገው ግብግብ በምንም መለኪያ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡
የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!