
ባሕር ዳር: ኅዳር 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት በከተማዋ ከሚገኙ ነጋዴዎች ጋር በመተባበር መሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርቡ እያደረገ መኾኑን የደሴ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ገለጿል።
በደሴ ከተማ የሚገኙ የኅብረት ሥራ ማኅበራት እና ዩኒኖች ያለባቸውን የገንዘብ እጥረት በመቅረፍ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚያደርግም የከተማዋ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ገልጿል።
እየተስተዋለ ያለውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት መምሪያው ከአራዳ ክፍለ ከተማ ንግድ ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር ቅን አሳቢ የሸርፍ ተራ ነጋዴዎችን በማወያየት መሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦችን በቅናሽ ዋጋ ለማኅበረሰቡ እንዲቀርቡ እያደረገ ይገኛል።
ምርቶችን ሲሸምቱ አሚኮ ያገኛቸው የደሴ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አበባ መኮንን እና አቶ ዘሩ አሠፋ የዋጋ ቅናሽ መኖሩን ጠቁመው የአቅርቦት እጥረት ስላለ ምርት በስፋት እንዲቀርብ ቢደረግ መልካም ነው ብለዋል። የእሁድ ገበያም ቢጀመር ሲሉ ጠይቀዋል ።
የምግብ ምርቶች ጅምላ አከፋፋይ ወጣት እንድሪስ አሕመድ እና ወጣት አብዱሠላም መኸዲ ሸቀጦች በዚህ ሁኔታ መቅረባቸው ለገበያ መረጋጋቱ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
የአራዳ ክፍለ ከተማ ምክትል ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ሥነወርቅ ዳኘ የንግዱን ማኅበረሰብ በማወያየት መሠረታዊ እቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ቀርበዋል ብለዋል።
ተሞክሮውን ወደ ሌሎች ክፍለ ከተሞች በማስፋት የአቅርቦት እጥረት ያለባቸውን ምርቶች በስፋት ለማቅረብ ይሠራል ያሉት ደግሞ የደሴ ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ዮናስ እንዳለ ናቸው።
በከተማ አሥተዳደሩ በኅብረት ሥራ ማኅበራት እና ዩኒኖች ላይ የሚስተዋለውን የገንዘብ እጥረት ለመቅረፍ ተዘዋዋሪ ብድር በማመቻቸት ማኅበራቱን ለማጠናከር እንደሚሠራም መምሪያ ኀላፊው ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ አንተነህ ፀጋዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!