“ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ ናት” አቶ ደመቀ መኮንን

77

አዲስ አበባ: ኅዳር 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ኅብረት ግንኙነታቸውን በሚያድሱበት ኹኔታ ላይ ምክክር እያካሔዱ ነው። ውይይቱን የመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን “ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ ናት”ብለዋል።

ኅብረቱ ለኢትዮጵያ በተለያዩ መንገዶች እገዛ ሲያደርግ መቆየቱን አንሰተው በተለይም በሰው ሃብት ልማት፣ በሃብት ፈጠራ እና በኢንተርፕራይዞች ልማት ያደረገው ድጋፍ ትልቅ ነው። ከዚህ ጥብቅ እና ቀደምት ግንኙነት በመነሳት ግንኙነታችን ማሻሻል እና ማጠናከር ከባድ አይሆንም ብለዋል።

የአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋት አሳስቦት በዚህ መልኩ ድጋፍ እና እጋዛ ለማድረግ ስለሻተ እናመሠግነዋለን ብለዋል። ከዚህ በፊት ስናደርግ እንደነበረው ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔን ለመስጠት በአፍሪካ ኅብረት ላይ መሠረት አድርገን እንሠራልን ነው ያሉት። እናንተን በአጋዥነት በቴክኒክ እና ሙያዊ ድጋፍ ታግዘን ችግሮችን እንፈታለን ብለዋል።

የአውሮፓ ኅብረት እና ኢትዮጵያ በጋራ የሚሠሯቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ ያሉት ሚኒስትሩ የዛሬው ውይይትም በዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዘርፈ ብዙ ግንኙነታችንን ያጠናክራል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ የውይይት ዓላማ ስትራቴጂክ የኾነውን የሁለትዮሽ ትብብር ማደስ እና ወደ መደበኛ ኹኔታ መመለስ ነው ብለዋል። የአውሮፓ ኅበረት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን እገዛ አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

እንደ አምባሳደር ሮላንድ ገለፃ የአውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ ከሚያደርገው ጠንካራ የዲፕሎማሲ እና ፖለቲካዊ ድጋፍ በተጨማሪ ስድስት በመቶ የውጭ ንግድ ከፍተኛ መዳረሻ መኾን የቻለ ነው ብለዋል። በኢንቨስትመንት ዘርፍ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው የኅብረቱ ሀገራት ኩባንያዎች በኢትዮጵያ 140 ቢሊዮን ዩሮ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ለ150 ሺህ ኢትዮጵያውያን የሥራ እድል መፍጠር ችለዋል ተብሏል። በልማት፣ ትብብር እና በመልሶ ግንባታ ዘርፎች በአንድ ዓመት ብቻ 350 ሚሊዮን ዩሮ ለኢትዮጵያ ድጋፍ መደረጉም ተነስቷል።

የአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ባከበረ መልኩ ሰላም፣ ፍትሕ እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ያግዛል ነው የተባለው። ባለፉት ሦስት ዓመታት የተጎዳውን ኢንቨስትመንት እና የንግድ እንቅስቃሴ እንዲሻሻል በዚህ መድረክ መወያየቱ እና መገምገሙ ያስፈልግ ነበር ብለዋል።

በጋራ ምክክር መድረኩ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የፍትሕ ሚኒስቴር እና የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል። በአውሮፓ ኅብረት በኩል በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር፣ የኅብረቱ አባል ሀገራት አምባሳደሮች እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አንድነታችን የአብሮነታችን እና የታሪካችን ምንጭ ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ
Next articleየኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት እየሰራ መኾኑን የደሴ ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ገለጸ።